Fana: At a Speed of Life!

ፊሊፒንስ ከአሜሪካ እና ሌሎች ምዕራባውያን አጋሮቿ ጋር የጀመረችው የጦር ልምምድ ቻይናን አስቆጣ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አሜሪካ፣ አውስትራሊያ፣ ካናዳ እና ፊሊፒንስ በአወዛጋቢው የደቡብ ቻይና ባህር ላይ የባህር ኃይል እና የአየር ሃይል የጦር ልምምዶችን ማድረግ መጀመራቸው ቻይናን አስቆጥቷል፡፡

ይህንንም ተከትሎ የቻይና ጦር ከፊሊፒንስ ጋር የይገባኛል ውዝግብ በሚያነሱበት በደቡብ ቻይና ባህር ወታደራዊ ልምምድ ማካሄድ ጀምሯል።

በተመሳሳይ ቀን መደረግ የጀመረው ልምምድ ፊሊፒንስ ከአሜሪካ እና ሌሎች ምዕራባውያን አጋሮቿ ጋር ለጀመሩት ወታደራዊ እንቅስቃሴ ምላሽ ለመስጠት ያለመ እንደሚመስልም ተመላክቷል፡፡

የደቡባዊው ልምምድ አዛዥ እንደገለፁት÷ የማጥቃት አቅምን ለመፈተሸ በሁንግያን ደሴት አቅራቢያ የአየር እና የባህር ሃይል ልምምድ ማድረግ ጀምረዋል፡፡

የቻይና ልምምዶች የወታደሮቿን የቅኝት እና የቅድመ ማስጠንቀቂያ አቅምን የፈተሹ መሆናቸውን ቤጂንግ ተናግራለች።

የደቡብ ቻይናን ባህር የሚያውኩ፣ የመገናኛ ቦታዎችን የሚፈጥሩ እና ቀጣናዊ ሰላምና መረጋጋትን የሚጎዱ ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች በሙሉ ከፍተኛ ደረጃ ቁጥጥር እየተደረገባቸው መሀኑንም ገልፃለች።

ከአሜሪካ፣ አውስትራሊያ፣ ካናዳ እና ፊሊፒንስ የተውጣጡ የጦር አዛዦች በጋራ ባወጡት መግለጫ÷ የጋራ የባህር ላይ ተግዳሮቶችን ለመፍታት በአንድነት መቆማቸውን አመላክተዋል፡፡

ዓለም አቀፍ ህግን እና መመሪያዎችን መሰረት ያደረገ ስርዓትን ለማስጠበቅ ያላቸውን የጋራ ቁርጠኝነትም በአጽንኦት ገልጸዋል።

ለሁለት ቀናት የሚቆዩት ልምምዶችም በእስያ ፓስፊክ ቀጣና ነፃ መተላለፊያን ለመጠበቅ የሚደረጉ ናቸው ማለታቸውን አልጀዚራ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.