Fana: At a Speed of Life!

ለጎፋ ዞን እስካሁን 210 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ መደረጉ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጎፋ ዞን በደረሰው የመሬት መንሸራተት አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች እስካሁን ቃል የተገባውን ሳይጨምር 210 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ መደረጉ ተገልጿል፡፡

ከተደረገው ድጋፍ ውስጥ 92 ነጥብ 5 ሚሊየን ብሩ በጥሬ ገንዘብ ሲሆን÷ከ118 ሚሊየን ብር በላይ የሚሆነው ደግሞ በአይነት የተደረገ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማትን ጨምሮ መላ ኢትዮጵያውያን ባደረጉት ርብርብ ለአደጋው ተጎጂዎች አስፈላጊ የሰብዓዊ ድጋፍ ማቅረብ መቻሉን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ተናግረዋል፡፡

የክልሉ መንግስት ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ዝርዝር ዕቅድ አዘጋጅቶ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን አንስተዋል፡፡

በዚህም የተፈናቀሉ ወገኖችንና የአደጋ ስጋት ተጋላጭ የሆኑ ዜጎች ከስጋት ቀጣና ውጪ በሆነ ቦታ በቋሚነት የማቋቋምና ወደ ቀደመ ሕይወታቸው የመመለስ ሥራ ቁልፍ ተግባር መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በድንገተኛ የመሬት መንሸራተት አደጋው ከ600 በላይ አባዎራዎች የተፈናቀሉ ሲሆን÷15 ሺህ ዜጎች ደግሞ በአካባቢው ለአደጋ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች እንደሚገኙ መለየቱ ተጠቁሟል፡፡

ለተጎጂዎቹ እስካሁን ቃል ከተገባው ውጪ 92 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር የገንዘብ እና ከ118 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የአይነት ድጋፍ መደረጉን የርዕሰ መስተዳድሩ ጽ/ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.