በኮሙኒኬሽን ዘርፍ የኢትዮጵያን ሃሳቦች ለዓለም የማስተዋወቅ ስራ በስፋት እንደሚሰራ ተመላከተ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በተያዘው በጀት ዓመት በሀገር ውስጥ የኮሙኒኬሽን ሥርአቱን ከማጠናከር ባለፈ የኢትዮጵያን ሀሳቦችና አቅሞች ለዓለም የማስተዋወቅ ስራ በስፋት እንደሚሰራ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴዔታ ሰላማዊት ካሳ÷ በተጠናቀቀው የ2016 በጀት ዓመት የተቋሙን አቅም ሚያጠናክሩ ሰፋፊ ስራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።
አገልግሎቱ የስራዎቹን አድማስ በማስፋት በዐበይት ሀገራዊ ሁነቶች ላይ ሰፊ ተሳትፎ ማድረጉን ነው የገለጹት።
የኮሙኒኬሽን መዋቅሩንና የመገናኛ ብዙሃንን አቅም የሚያሳድጉ ተግባራት መከናወናቸውን አስረድተዋል፡፡
ለአብነትም ለህዝብና ለንግድ መገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችና አመራሮች የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች መሰጠታቸውን ጠቅሰው፤ ከመገናኛ ብዙሃን ጋር ቋሚ የግንኙነት ስርዓት በመዘርጋት መረጃዎችን በመደበኛነት ተደራሽ የማድረግ ስራ ተከናውኗል ብለዋል።
በተጨማሪም መገናኛ ብዙሃንን በማስተባበር በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የተከናወኑ የልማት ስራዎች ምልከታ መደረጉን ጠቁመዋል።
በ2017 በጀት ዓመት ሀገራዊ አቅሞችን በማውጣት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ስራዎች በትኩረት እንደሚሰሩ አመላክተዋል።
በተጨማሪም የኮሙኒኬሽን ስርአቱን የማጠናከርና አድማሱን የማስፋት ስራ በመስራት የተጽእኖ አድማስን በማሳደግ በአፍሪካ ብሎም በዓለም መድረኮች የኢትዮጵያን ሀሳብና አቅም የማስተዋወቅ ስራ በትኩረት እንደሚሰራ ለኢዜአ ተናግረዋል።
መገናኛ ብዙሃን ሁሉንም ተደራሽ ያደረጉ የይዘት ስራዎችን ታች ድረስ ወርደው እንዲያከናውኑ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ጠቁመዋል።