ችግር ፈቺ በሆኑ የፈጠራ ሥራዎች ላይ የተሰማሩ አካላት ልዩ ድጋፍ ይደረግላቸዋል – አቶ ጌታቸው ረዳ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በትግራይ ክልል ችግር ፈቺ በሆኑ የፈጠራ ሥራዎች ላይ የተሰማሩ አካላት ልዩ ድጋፍ እንደሚደረግላቸው የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር አስታወቀ።
በሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲሁም በምርምርና ፈጠራ ሥራዎች ረገድ ለሚያጋጥሙ ችግሮች የመፍትሄ አቅጣጫን ለማመላከት ያለመ የባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ ተካሂዷል፡፡
በመድረኩ ላይ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር ጌታቸው ረዳ እንደገለጹት÷ ችግር ፈቺ በሆኑ የፈጠራ ሥራዎች ላይ የተሰማሩ አካላት ልዩ ድጋፍ ይደረግላቸዋል።
በክልሉ የሳይንስና ቴክኖሎጂ የፈጠራ ሥራዎችን በተቀናጀ መልኩ አደራጅቶ ወደ ተግባር ለመቀየር ያለመቻል ክፍተት መኖሩን አመልክተዋል፡፡
የመድረኩ ዋና ዓላማም በፈጠራ የተሰማሩ ወጣቶችን ለማበረታታትና ድጋፍ ለማድረግ እንደሆነ ገልፀው÷ ሥራዎቻቸውን ወደ ተግባር በመቀየር የማህበረሰቡን ችግር እንዲፈቱ ለማድረግ መሆኑንም አክለዋል።
”ከተረጂነት ተላቀን ራሳችንን እንድንችል ዘመናዊ እርሻን ማስፋፋት አለብን” ያሉት አቶ ጌታቸው÷ በተለይ የአርሶ አደሩን ሕይወት ለሚቀይሩ የእርሻ ሜካናይዜሽን የፈጠራ ሥራዎች ልዩ ድጋፍ እንደሚደረግ ተናግረዋል።
የህዝብ አኗኗር የሚቀየረው እና ልማት የሚያድገው በፈጠራና በምርምር ሥራዎች በመሆኑ ለሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ልዩ ትኩረት እንደሚሰጥም ተናግረዋል፡፡
በዩኒቨርሲቲዎችና በምርምር ተቋማት የሚገኙ ምሁራን ለዘርፉ ትኩረት በመስጠት መስራት እንደሚጠበቅባቸው ማስገንዘባቸውንም ኢዜአ ዘግቧል፡፡