ባንኮች አጠራጣሪ ግብይቶችን በወቅቱ ሪፖርት በማድረግ የፋይናንስ ወንጀሎችን ለመከላከል የበኩላቸውን መወጣት አለባቸው ተባለ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ባንኮች አጠራጣሪ ግብይቶችን በአግባቡና በወቅቱ ሪፖርት በማድረግ የፋይናንስ ወንጀሎችን ለመከላከል የበኩላቸውን መወጣት እንዳለባቸው የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ገለጸ።
ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውርን ለመከላከል የሚያስችል የፋይናንስ አገልግሎት ተቋማት የውይይት መድረክ በአዲስ አበባ ተካሂዷል፡፡
የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሙሉቀን አማረ በመድረኩ ላይ÷ መንግስት ማሻሻዎችንና የለውጥ ርምጃዎች መውሰዱን አንስተው÷ በቅርቡ ወደ ተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ገብተናል ብለዋል፡፡
በሕገ-ወጥ መንገድ የተገኙ ገንዘቦችን ሕጋዊ የማድረግ እንቅስቃሴዎች መኖራቸውንም ገልጸው፤ ገንዘቦቹ በባንክ ሥርዓት ውስጥ የሚያልፉበት አጋጣሚ መኖሩን ጠቅሰዋል።
ባንኮች አጠራጣሪ ግብይቶችን በአግባቡና በወቅቱ ለፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት በማሳወቅ ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል ሲሉም አስገንዝበዋል።
በአንዳንድ የባንክ ባለሙያዎች ዘንድ የሚስተዋለውን የሥነ-ምግባር ግድፈት ጨምሮ በጥናት የታዩ ክፍተቶች እንዳሉና በቀጣይም እንደሚሰራባቸው አመላክተዋል፡፡
በወንጀል የተገኘ ገንዘብ የፋይናንስ ስርዓትና የድርጅቶች አለመረጋጋትን ከመፍጠሩ ባሻገር የውጭ ኢንቨስትመንት ላይም ጫና እንደሚፈጥር እንዲሁም ዓለም አቀፍ የንግድ ስርዓትንም እንደሚያዛባ በመድረኩ ተገልጿል፡፡
ወኪልንና የዓለም አቀፍ የገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶችን በመጠቀም የሚፈጸም የሃዋላ ወንጀል የህግ ወጥ የገንዘብ ዝውውር መስፋፋት ማሳያዎች ናቸውም ተብሏል፡፡
በየሻምበል ምህረት