ለሀገሩ ዋጋ የከፈለ ሠው ማንም ቢሆን የተከበረ ነው – ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ለሀገሩ ዋጋ የከፈለ ሠው ማንም ቢሆን የተከበረ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው÷ የሀገር መከላከያ ሠራዊት በለውጥ ንቅናቄ የተጓዘባቸውን መንገዶች በተመለከተ ከመንግስት ከፍተኛ አመራሮች ጋር የጋራ አረዳድ ለመፍጠር የተዘጋጀው መድረክ የተሳካ ነበር ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ታሪክ ዋነኛ መሠረቱ ወታደር መሆኑን ጠቅሰው÷ አይተኬ ህይወቱን ገብሮ ሀገርና ትውልድ ያጸናል፤ ከሠፈርና ከመንደር የተሻገረ የላቀ አላማ እና መስዋዕትነት የያዘ ሠራዊት ሀገርን ይታደጋልም ነው ያሉት፡፡
የሀገር መከላከያ ሠራዊት በየደረጃው የገጠመው ፈተና የተሻለ ደረጃና አቅም ያለው ሆኖ ዳግም እንዲፈጠር አስችሎታል፤ ይህን አቅሙን በመጠቀም በበለጠ ፍቅርና ታማኝነት ሊያገለግል ይገባልም ብለዋል፡፡
የሀገር መከላከያ ሠራዊት በለውጥ ንቅናቄ የተጓዘባቸውን መንገዶች በተመለከተ ከመንግስት ከፍተኛ አመራሮች ጋር የጋራ አረዳድ ለመፍጠር የተዘጋጀው መድረክ የተሳካ ነበርም ሲሉ ገልጸዋል፡፡