የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ (ህ.ወ.ሓት) ጠቅላላ ጉባዔውን ሊያደርግ መሆኑን በመገናኛ ብዙኃን መነገሩን ተከትሎ ቦርዱ ለፓርቲው የጻፈው ደብዳቤ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህ.ወ.ሓት) ጠቅላላ ጉባዔውን ሊያደርግ መሆኑን በመገናኛ ብዙኃን መነገሩን ተከትሎ ቦርዱ ለፓርቲው የጻፈው ደብዳቤ እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
ለሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህውሓት)
መቐለ
ጉዳዩ ፡- ፖርቲው ጠራ የተባለውን ጠቅላላ ጉባዔ ይመለከታል
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ነሐሴ 3 ቀን 2016 ዓ.ም በቁጥር አ1162/11/15180 ለፓርቲው በጻፈው ደብዳቤ ፓርቲው በልዩ ሁኔታ መመዝገቡን ገልጿል፡፡የህጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀትም ተሰጥቷል፡፡
ፓርቲው ከፍብሎ የተጠቀሰው የቦርዱ ደብዳቤና የምስክር ወረቀት ከደረሰው ቀን ጀምሮ የሚተዳደረው የኢትዮጵያ የምርጫ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 እና ይህን አዋጅ ባሻሻለው አዋጅ ቁጥር 1332/2016 እንዲሁም እነዚህን አዋጆች መሰረት ተደርገው በወጡ መመሪያዎች እና የቦርዱ ውሳኔዎች መሰረት ነው፡፡
ቦርዱ ውሳኔ የሰጠባቸውና በደብዳቤው ከገለፃቸው በፓርቲውመተግበር ካለባቸው ተግባራት መካከል ፓርቲው ጠቅላላ ጉባዔ ከማድረጉ ከ21 ቀን በፊት ለቦርዱ ማሳወቅና ፓርቲው በሚያደርገው ጠቅላላ ጉባዔ የቦርዱ ታዛቢዎች መገኘት በዋናነት የተገለፁ ግዴታዎች ናቸው ፡
ሆኖም ግን በአሁኑ ወቅት ፓርቲው ጠቅላላ ጉባዔ ሊያደርግ መሆኑን ቦርዱ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን እየተዘገበ መሆኑ ተመልክቷል፡፡
ስለዚህ ቦርዱ ለአንድ ጠቅላላ ጉባዔ መደረግ አስፈላጊ የሆኑ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን እንዲያውቅ ባልተደረገበት፣ባልተከታተለበትና ባላረጋገጠበት እንዲሁም የቦርዱ ታዛቢዎች ባልተገኙበት ተጠራ የተባለው ጠቅላላ ጉባዔ ሊካሄድ አይችልም፡፡
ጠቅላላ ጉባዔው ከቦርዱ ፍቃድ ውጭ ከተካሄደም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለዚህ ጉባዔም ሆነ በጉባዔዎቹ ላይ ለሚወሰኑ ውሳኔዎች በሙሉ ዕውቅና የማይሰጥ መሆኑን ከወዲሁ በአክብሮት እናሳውቃለን፡፡
ከአክብሮት ሰላምታ ጋር
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ