Fana: At a Speed of Life!

በጣና ሃይቅ ላይ የተከሰተውን የእምቦጭ አረም ለመቆጣጠር እና ለመግታት የመፍትሄ እርምጃዎችን ተግባራዊ የማድረግ ጥረቱ ይቀጥላል – አቶ ደመቀ መኮንን

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 15፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በጣና ሃይቅ ላይ የተከሰተውን የእምቦጭ አረም ለመቆጣጠር እና ለመግታት መንግሥት የመፍትሄ እርምጃዎችን በተጠና አግባብ ተግባራዊ የማድረግ ጥረቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን አስታወቁ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጨምሮ የፌደራል እና የአማራ ክልል ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ሃላፊዎች በደቡብ ጎንደር ዞን ሊቦ ከምከም ወረዳ ቅርኛ ቀበሌ ተገኝተው በጣና ሐይቅ ላይ የተጋረጠውን የእምቦጭ አረም አደጋ ተመልክተዋል።

አቶ ደመቀ የእምቦጭ አረምን ለመቆጣጠር መንግሥት የመፍትሄ እርምጃዎችን በተጠና አግባብ ተግባራዊ የማድረግ ጥረቱን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በጣና ሐይቅ ላይ የተከሰተውን የእምቦጭ አረም በዘላቂነት ለማስወገድ የሚያስችል የረጅም እና የአጭር ጊዜ የመፍትሔ እርምጃ ተግባራዊ ይደረጋልም ነው ያሉት።

በጣና ሃይቅ ህልውና ላይ የተደቀነውን ስጋት ወደ ለየለት የተፈጥሮ ቀውስ እንዳያመራ የፌደራል መንግሥት ችግሩን ለመፍታት የሚያስችሉ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ሃገሪቱ ካሏት ታላላቅ የተፈጥሮ ፀጋዎች መካከል የጣና ሃይቅ ህብረ ብዙ ፋይዳ በውስጡ መያዙን ጠቁመው የሃይቁን ደህንነት እና ጤንነት በማስጠበቅ ረገድ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

በአሁኑ ጊዜ እየተወሰደ ያለው የመፍትሔ አማራጭ አደጋውን በመቀነስ ረገድ አጋዥ ፋይዳ ቢኖረውም፤ በዘላቂነት አረሙን ከሐይቁ ለማስወገድ የተቀናጀ ርብርብ እንደሚያፈልግ አስምረውበታል፡፡

የጣና ሃይቅን ዕምቅ ፀጋ ለመጠቀም እና የአካባቢውን ነዋሪዎች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የመሠረተ ልማት ጥያቄዎች በዕቅድ ይመለሳሉ ማለታቸውን ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.