ከ215 ሺህ በላይ የታዳሽ ኃይል ቴክኖሎጂዎች ለሕብረተሰቡ ተደራሽ ሆኑ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በ2016 ዓ.ም ከ215 ሺህ በላይ የታዳሽ ኃይል ቴክኖሎጂዎችን ለሕብረተሰቡ ተደራሽ ማድረጉን የአማራ ክልል ውኃና ኢነርጂ ቢሮ አስታወቀ።
ቴክኖሎጂዎቹ የገጠሩን ማኅበረሰብ የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል የሚያግዙ መሆናቸውን የቢሮው ምክትል ኃላፊ ጥላሁን ሽመልስ ገልጸዋል፡፡
ከተሰራጩት የታዳሽ ኃይል ቴክኖሎጂዎች መካከል በፀሐይ ኃይል የሚሠሩ ከ82 ሺህ በላይና ከ28 ሺህ በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል ቆጣቢ ምድጃዎች እንደሚገኙበት ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም ከ1 ሺህ 893 በላይ የባዮ ጋዝ ቴክኖሎጂዎችን በማስገንባትና ከ103 ሺህ 400 በላይ የተሻሻሉ ማገዶ ቆጣቢ ምድጃዎችን ለገጠሩ ማኅበረሰብ ተደራሽ ተደርጓል ብለዋል፡፡
በዚህም ከ646 ሺህ 370 በላይ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ጠቅሰው÷ በክልሉ የታዳሽ ኃይል ቴክኖሎጂ ተደራሽነት 69 በመቶ መድረሱን አመላክተዋል፡፡