ኢትዮጵያና የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች በኦዲት ዘርፍ በትብብር ለመስራት ተስማሙ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌዴራል ዋና ኦዲተር ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ ከተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች ዋና ኦዲተር ተቋም ሃላፊ ሐሚድ አቡሺቢስ ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸውም÷ ሁለቱ ተቋማት በጋራ በሚሰሩባቸው የኦዲት እና ተዘማጅ ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል፡፡
የሀገራቱ ዋና ኦዲተር ተቋማት በቀጣይ በሚያከናውኗቸው የጋራ ሥራዎች እና የልምድ ልውውጦች ላይ በትብብር ለመስራት ስምምነት ላይ መድረሳቸው ተገልጿል፡፡
በተለይም በሥልጠና ተቋምና በአቅም ግንባታ፣ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ኦዲት፣ የተለያዩ ወርክሾፖችንና ሴሚናሮችን በማዘጋጀት እና በሌሎች ዘርፎች ዙሪያ በጋራ ለመስራትና ለመደጋገፍ ተስማምተዋል፡፡
የስምምነት ትግበራውን የሚያመቻችና የሚከታተል የቴክኒክ ኮሚቴ ለማቋቋም ስምምነት ላይ መድረሳቸውንም የፌዴራል ዋና ኦዲተር መረጃ ያመላክታል፡፡