እዳውን የመቀነስ፤ ምንዳውን የመጨመር ታሪካዊ ሃላፊነት ተጥሎብናል – አቶ አረጋ ከበደ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) እዳውን የመቀነስ፤ ምንዳውን የመጨመር ታሪካዊ ሃላፊነት ተጥሎብናል ሲሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ገለጹ፡፡
አቶ አረጋ በዞኖች እና ከተማ አሥተዳደሮች ደረጃ የሚካሄደውን የ2016 እቅድ አፈጻጸም ግምገማ እና የ2017 በጀት ዓመት እቅድ ትውውቅ መድረክ አስጀምረዋል፡፡
ርዕሰ መሥተዳድርሩ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ የ2016 በጀት ዓመት አፈጻጸምን በእውነት፣ በቅንነት እና በመርሕ ላይ ተመሥርቶ መገምግም ለ2017 እቅድ ትግበራ የጋራ መግባባት ላይ ለመድረስ ያግዛል፡፡
ክልሉ ላለፈው አንድ ዓመት የቆየበት ነባራዊ ሁኔታ ግልጽ ነው” ያሉት አቶ አረጋ÷ በክልሉ ሰላም እና ጸጥታ ሥራዎች ዙሪያ እውነት ላይ የተመሠረተ ውይይት ማድረግ እንደሚያስፈልግ አንስተዋል፡፡
በክልሉ የነበረው የሰላም እጦት በምጣኔ ሃብታዊ፣ ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ ዘርፎች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳሳደረም አስገንዝበዋል፡፡
ለዚህም ዙሪያ መለስ ግምገማ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመው÷ ካለፈው ዓመት እቅድ አፈጻጸም ግምገማና ውይይት በኋላ በመጪው ዓመት እቅድ ላይ መግባባት መድረስ እንደሚያስፈልግ መናገራቸውን አሚኮ ዘግቧል፡፡