ለአንድ ጀንበር የችግኝ ተከላ መርሐ-ግብር ዝግጅት ተጠናቀቀ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የፊታችን ነሐሴ 17 ቀን 2016 ዓ.ም ለሚከናወነው የአንድ ጀንበር የችግኝ ተከላ መርሐ-ግብር አስፈላጊው ዝግጅት መጠናቀቁን ግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ባስቀመጡት አቅጣጫ መሠረት በአንድ ጀንበር 600 ሚሊየን ችግኞችን በ325 ሺህ ሄክታር ላይ ለመትከል ዝግጅት መጠናቀቁን የግብርና ሚኒስትር ዴዔታ ኢያሱ ኤልያስ (ፕ/ር) ገልጸዋል፡፡
ችግኞቹ በ5 ሺህ 456 ተፋሰሶች ላይ እንደሚተከሉ እና የካርታ ዝግጅት ሥራውም መጠናቀቁን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል፡፡
ባለፈው ዓመት በአንድ ጀንበር 550 ሚሊየን ችግኞች መተከላቸውንና 34 ሚሊየን ሕዝብ መሳተፉን አስታውሰው÷ ዘንድሮ በአንድ ጀንበር 600 ሚሊየን ችግኞችን ለመትከል 30 ሚሊየን ሕዝብ እንደሚሳተፍ ይጠበቃል ብለዋል፡፡
በዕለቱም መረጃ የሚያቀብሉ ባለሙያዎች ስልጠና መውሰዳቸውን እና በየሰዓቱ የሚወጡ መረጃዎችን መከታተል የሚያስችል ኢትዮ ግሪን ሌጋሲ (Ethio green legacy) የተሰኛ ፖርታል መበልጸጉን ጠቁመዋል።
ሕዝቡ በነቂስ በመውጣት የሀገራችንን ዲፕሎማሲ፣ የውሃና የምግብ ዋስትናችንን በምናረጋግጥበት መርሐ-ግብር ዐሻራውን እንዲያኖር ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
በመሳፍንት እያዩ