የአማራ ክልልን ከስጋት ወጥቶ ወደ ብልጽግና ለማሻገር የክልሉ አመራር ቁርጠኛነቱን እያሳየ ነው – ም/ጠ/ሚ ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ክልልን ከግጭትና ከጸጥታ ስጋት ወጥቶ ወደ ብልጽግና ለማሻገር የክልሉ አመራር ቁርጠኛነቱን በተግባር እያሳየ ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተገኙበት የክልሉ የ25 ዓመት የማክሮ ኢኮኖሚ ፍኖተ ካርታና ከዚሁ የተቀዳው የ5 አመት ስትራቴጂክ እቅድ የምክክር መድረክ እየተካሄደ ነው።
ምሁራንና ባለሙያዎች የተሳተፉበት የአሻጋሪ ዕድገትና የዘላቂ ልማት እቅዱ በቀውስ ውስጥ አልፈው የተሻገሩ ሀገራት ተሞክሮ የተካተተበትና አሻጋሪ እውቀትና አቅም የታከለበት መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንስተዋል።
ህዝቡ ከግጭትና ከችግር ወጥቶ ወደ ብልጽግና የሚሻገርበት ታሪካዊ ምክክር ነው ያሉት አቶ ተመስገን÷ ፍኖተ ካርታው ማህበረሰቡንና ሀገሩን መጥቀምና እድገቱን የሚፈልግ እውቀቱን የሚያዋጣበት እድል መሆኑንም ጠቁመዋል።
የዚህ መድረክ ዓላማ ፍኖተ ካርታውን እና ከዚሁ ተቀድቶ የተዘጋጀውን የ5 አመት ስትራቴጅክ እቅድ ማስተቸት፣ እቅዱን የሚያዳብሩ ግብአቶችን ማሰባሰብ፣ በቀጣይ በትግበራ ወቅት አመራሩ ባለቤት ሆኖ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ መፍጠር እንደሆነ ተገልጿል።
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ በበኩላቸው÷ በምክክሩ የተሳተፉ አመራሮችን የተጠናከረ ድጋፍና ትብብርን ጠይቀዋል፡፡
ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥና ልማት እንዲጠናከር አዎንታዊ ፍላጎት ያለው አመራር በመሆኑ በአጭር ጊዜ ለውጥ እንደሚመጣ እምነታቸውን ገልጸዋል።
ፍኖተ ካርታው ለቀጣይ 6 ወራት በተለያዩ አካላት በውይይት እንደሚዳብርም ተጠቁሟል።
ክልሉ የ2017 በጀት አመትን ጨምሮ በቀጣዩ የ5 አመት ስትራቴጅክ ዘመን የ10 ነጥብ 6 በመቶ አማካኝ የኢኮኖሚ እድገት ለማስመዝገብም እንዳቀደ ተገልጿል፡፡
ይህን ለማሳካት የግብርና ዘርፍ ከፍተኛ ድርሻ የሚጠበቅበት ይሆናል ተብሏል።
የኢኮኖሚ እድገቱ እውን እንዲሆን ሁሉም አካላት ልምዳቸውን ተጠቅመው እቅዱን በጥብቅ ዲስፕሊን አመራር ሲሰጡ ብቻ ስለሆነ ለዚሁ ተግባራዊነትም የክልሉና የፌዴራል መንግስቱ አመራሮች ሃላፊነት እንዳለባቸው ተመላክቷል።
ከ2018 እስከ 2042 ዓ.ም በተዘጋጀው ፍኖተ ካርታ በ2042 የአማራ ብሔራዊ ክልል በዓለም በቴክኖሎጂ ተወዳዳሪ የሆነ የዘመናዊ ኢኮኖሚ አቅም ባለቤት ሆኖ ማየት የሚል ራዕይ የያዘ ነው።
በፍሬህይወት ሰፊው