Fana: At a Speed of Life!

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልልን በማጠናከር ሂደት የሕዝቡ አጋርነት እንዲጠናከር ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፈው ዓመት የተመሠረተውን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በማጠናከር ሂደት የመላው ሕዝብ ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የክልሉ መንግሥት ጥሪ አቀረበ፡፡

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የተመሠረተበትን 1ኛ ዓመት አስመልክቶ የክልሉ ርዕሰ መሥተዳድር ጥላሁን ከበደ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በመልዕክታቸውም÷ የክልሉ መንግሥት ከምስረታ ማግስት ጀምሮ የሽግግር ጊዜና መደበኛ የልማትና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎች ዕቅድ አዘጋጅቶ በሠራው ሥራ በየዘርፉ ስኬቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል፡፡

ክልሉን የሰላም፣ የመቻቻልና የብልጽግና ተምሳሌት የማድረግ ራዕይ በመሰነቅ፣ የክልሉን ፀጋና እምቅ አቅም ታሳቢ ባደረገ መልኩ በተሠሩ ሥራዎች በሁሉም የልማት መስኮች አመርቂ ውጤት ተመዝግቧል ብለዋል፡፡

በቀጣይ በየዘርፉ የተጀመሩ የልማትና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎችን በኅብረተሰቡ የነቃ ተሳትፎ እና በአመራሩ ቁርጠኝነት ከዳር በማድረስ÷ የክልሉን ሕዝብ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ በጋራ የመልማት ፍላጎት ዕውን ለማድረግ የተቀናጀ ርብርብ እንደሚደረግ አመላክተዋል፡፡

መላው ሕዝባችንም እንደተለመደው ከክልሉ መንግሥት ጎን በመሰለፍ በአብሮነት የምንገነባው፣ በወንድማማችነት የምናፀናው፣ በፍቅር የምናሻግረው ክልል መሆኑን ተገንዝቦ÷ ባለቤትነቱን እና አጋርነቱን አጠናክሮ እንዲቀጥል ሲሉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.