የሽግግር ፍትሕ ትግበራ ፍኖተ-ካርታ ዝግጅት ተጠናቀቀ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢፌዴሪ የሽግግር ፍትሕ ትግበራ ፍኖተ-ካርታ ዝግጅት ተጠናቅቆ ወደ ሥራ መገባቱን የፍትሕ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
ሚኒስቴሩ ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ÷ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ሚያዝያ 9 ቀን 2016 ዓ.ም በሚኒስትሮች ም/ቤት መፅደቁን ተከትሎ ፖሊሲውን ወደ ትግበራ ምዕራፍ ለማሸጋገር የሚረዱ የቅድመ-ዝግጅት ስራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል፡፡
ከነዚህ ሥራዎች መካከል አንዱ የሆነው የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲውን አፈፃፀም፣ ክትትልና ድጋፍ ሥርዓት የሚመራ ፍኖተ ካርታ የማዘጋጀት ሥራ ተጠናቆ ወደ ሥራ እንዲገባ መደረጉ ተመላክቷል፡፡
በሌላ በኩል የሽግግር ፍትህ ፖሊሲው ካስቀመጣቸው ጉዳዮች አንዱ የሽግግር ፍትሕ ስልቶችን የሚተገብሩ ነጻ እና ገለልተኛ ተቋማት ለማቋቋምና ለማደራጀት የሚያስፈልጉ የተለያዩ የሕግ ማዕቀፎች ዝግጅትን የሚመለከት መሆኑ ተጠቁሟል።
በዚህ መሰረት የዓለም አቀፍ ወንጀሎችን የሚደነግግ አዋጅ፣ የእውነት ምህረት እና ማካካሻ ኮሚሸን ማቋቋሚያ አዋጅ እና የሌሎች የሽግግር ፍትሕ አላባዎች ፈፃሚ ተቋማት ማቋቋሚያ አዋጆችን የማርቀቅ ሥራ እየተሳለጠ ነው ተብሏል።
በተጨማሪም በሽግግር ፍትሕ ማዕቀፍ የወንጀል ጉዳዮችን የሚያየው ልዩ ችሎት ስልጣንና አሰራርን የሚመሰርተው የሽግግር ፍትሕ ልዩ ችሎት አዋጅ ዝግጅት በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አስተባባሪነት እንደሚከናወን ተገልጿል፡፡
የሕግ ማዕቀፎቹ ዝግጅት በጉዳዩ ላይ በቂ እውቀትና ልምድ ባላቸው ባለሙያዎች የሚካሄድ ሲሆን÷ አጠቃላይ ሒደቱ በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ተጠቁሟል።
የህግ ማርቀቅ ሥራው እንደተገባደደ ህዝቡና ባለድርሻ አካላት ዝርዝር አስተያየት የሚሰጡባቸው ሀገር-አቀፍ እና ዓለም አቀፍ መድረኮች እንደሚዘጋጁም ተጠቅሷል፡፡
የሕጎቹ በፍጥነት መውጣት በፖሊሲው ላይ የተመላከቱትን ዓላማዎች ለማሳካት እንደሚያስችሉ ተገልጿል።
በተለይም የተለያዩ የሽግግር ፍትሕ ስልቶችን በመጠቀም እውነት ለማውጣት፣ እርቅ የሚወርድበትን አሰራር ለመመስረት፣ የወንጀል ተጠያቂነትን ለማስፈን፣ በቅድመ-ሁኔታ ላይ የተመሰረተ ምህረትን ተግባራዊ ለማድረግ የማካካሻና ተቋማዊ ማሻሻያ ሥራዎችን ለማከናወንና የተሟላ ፍትህ ለማስፈን ቁልፍ ሚና እንደሚጫወቱ ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡