የውጭ ምንዛሪ አሥተዳደር ማሻሻያው ለፋይናንስ ተቋማት ዕድገት በር መክፈቱ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲን ተከትሎ ብሔራዊ ባንክ የወሰደው የውጭ ምንዛሪ አሥተዳደር ማሻሻያ ለፋይናንስ ተቋማት ዕድገት በር የከፈተ ወሳኝ ርምጃ መሆኑን የባንክ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች ገለጹ።
ገበያ መር የውጭ ምንዛሪ ተመን ሥርዓት ተግባራዊ መደረጉ ከባንኮች ባለፈ ለሀገር ኢኮኖሚ የዕድገት በር የከፈተ ወሳኝ ርምጃ መሆኑን በአዋሽ ባንክ ቺፍ ትራንስፎርሜሽን ኦፊሰር ተመስገን ቡሻ ተናግረዋል።
በአማራ ባንክ የስትራቴጂና ኢኖቬሽን ቺፍ ኦፊሰር እንዳልሽ ወልደሚካኤል በበኩላቸው÷ በማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ መነሻነት ገበያ መር የውጭ ምንዛሪ ተመን ሥርዓት መተግበሩ ለባንክ ኢንዱስትሪው ትልቅ ዕድል ነው ብለዋል።
የውጭ ምንዛሪ ተመን ሥርዓቱም ለገበያ ክፍት መደረጉ ከባንክ ዘርፍ ተወዳዳሪነት ባሻገር የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል።
በማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያው መነሻነት ባንኮች ተወዳዳሪነታቸውን ማስቀጠል የሚያስችል ሥራ እንደሚበቅባቸው ያመላከቱት ደግሞ በአሃዱ ባንክ የቺፍ ስትራቲጂ ኦፊሰር ፍቅሩ ወልደትንሳኤ ናቸው፡፡
ገበያ መር የውጭ ምንዛሪ ተመን ሥርዓት መዘርጋቱ ጤናማ የኢኮኖሚ ሥርዓት በመፍጠር በመደበኛና በትይዩ ገበያ መካከል ያለው የውጭ ምንዛሪ ተመን እንዲጣጣም ያስችላል ሲሉም ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡