ከግጭት አስተሳሰብ በመውጣት ትኩረትን ሰላምና ልማት ግንባታ ላይ ማዋል ይገባል- ወ/ሮ አለሚቱ ኡሞድ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አለሚቱ ኡሞድ በጋምቤላ ከተማ ከሚገኙ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ተወያይተዋል፡
የውይይቱ ተሳታፊዎች÷ሰላምን ማስፈን ለመንግስት ብቻ የሚተው ባለመሆኑ ከአመራሮች ጋር በትብብር እንሰራለን ብለዋል፡፡
መንግስት ሕዝቡ የሚያነሳቸውን የመሰረተ የልማት ጥያቄዎች ለመመለስ በትኩረት እንዲሰራም ጠይቀዋል።
ወ/ሮ አለሚቱ ኡሞድ በበኩላቸው÷ ሕዝባችን ከግጭት አስተሳሰብ ወጥቶ ትኩረቱን ለሰላምና ልማት ግንባታ ማድረግ ይጠበቅበታል ብለዋል።
ክልሉ ሰላም የሰፈነበት እና ልማት ያለበት እንዲሆን ሕዝቡ የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።
አዲሱ አመራር የህዝብን አንገብጋቢ ጥያቄዎች ለመመለስ ችግሮችን በመለየት ቅድሚያ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ማረጋገጣቸውንም የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡
በመድረኩ የሃገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ሴቶች፣ የቀበሌ ሊቀመናብርት፣ ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።