Fana: At a Speed of Life!

“በአንድ መጽሐፍ ለአንድ ተማሪ” ኢንሼቲቭ የታተሙ መጻሕፍት ሥርጭት ተጀመረ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል “በአንድ መጽሐፍ ለአንድ ተማሪ” ኢንሼቲቭ የገንዘብ ድጋፍ የታተሙ መጻሕፍት ሥርጭት ተጀመረ፡፡

የክልሉ ርዕሰ መሥተዳድር ጥላሁን ከበደ በተገኙበት የሥርጭት ማስጀመሪያ መርሐ-ግብር በወላይታ ሶዶ ከተማ ሊጋባ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተካሂዷል፡፡

በዚሁ ወቅት አቶ ጥላሁን “ለአንድ ተማሪ አንድ መጽሐፍ” ኢኒሼቲቭ ድጋፍ ያደረጉ የሕብረተሰብ ክፍሎችን አመስግነው÷በዋናነት ትምህርት ላይ ካልሰራን ብልፅግናን ዕውን ማድረግ አንችልም ብለዋል።

በትምህርት ላይ ያጋጠመንን ስብራት ለመፍታት ከመምህራን፣ ወላጅ እና ተማሪዎች ጋር በቅንጅት መስራት ይጠበቅብናል ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡

በቀጣይም ትምህርት ቤቶችን መጠገን ጨምሮ ሌሎች አስፈላጊ የትምህርት ቁሳቁሶችን ለማሟላት የክልሉ ሕዝብ እንዲረባረብ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በዛሬው ዕለት ለሥርጭት የበቁት መጻሕፍት ርዕሰ መሥተዳድሩ ያቀረቡትን ጥሪ ተከትሎ በክልሉ የሚገኙ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ባደረጉት የገንዘብ ድጋፍ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በዚሁ መሠረት ከ220 ሚሊየን ብር በሚልቅ ወጪ የታተሙ 1 ሚሊየን 540 ሺህ 192 መጻሕፍት በመጀመሪያው ዙር ለየዞኑ መሠራጨታቸውን የርዕሰ መሥተዳድር ጽሕፈት ቤት መረጃ አመላክቷል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.