ክልሉ በሀገር አቀፍ ደረጃ በአንድ ጀምበር ለሚከናወነው ችግኝ ተከላ ዝግጅቱን አጠናቀቀ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከነገ በስቲያ በሀገር አቀፍ ደረጃ በአንድ ጀምበር ለሚከናወነው የችግኝ ተከላ መርሐ-ግብር የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዝግጅት ማጠናቀቁን አስታወቀ፡፡
በዚህም የተከላ ቦታ ልየታ፣ የጉድጓድ ቁፋሮ፣ የችግኝ ዓይነትና መጠን መጠናቀቁ የተገለጸ ሲሆን÷ በዕለቱም የደን፣ የፍራፍሬ፣ የውበትና የጥላ ዛፎች እንደሚተከሉ ተመላክቷል፡፡
በተለዩ 553 ቦታዎች ተከላው እንደሚከናወን የገለጹት የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ሰናይት ሰለሞን÷ ከ3 ሺህ 944 ሔክታር በላይ መሬት በችግኝ ተከላው ይሸፈናል ብለዋል፡፡
በጂኦፖርታል የመረጃ ሥርዓት ቦታዎች ላይ ሆነው ሪፖርት ለሚያቀርቡ ባለሙያዎች ስምሪት መሰጠቱን ጠቅሰው÷ በተከላው ከ2 ነጥብ 2 ሚሊየን ሕዝብ በላይ እንደሚሳተፍ ይጠበቃል ብለዋል፡፡
ነሐሴ 17 ቀን 2016 ዓ.ም በአንድ ጀምበር 600 ሚሊየን ችግኞችን ለመትከል የቀረበውን ሀገራዊ ጥሪ ተከትሎ በተለያዩ አካባቢዎች የዝግጅት ሥራዎች እየተጠናቀቁ መሆኑ ይታወቃል፡፡