የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ልጇን በግፍ ለተነጠቀቸው ሕጻን ሄቨን እናት የመኖሪያ ቤት አበረከተ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ልጇን በግፍ ለተነጠቀቸው ሕጻን ሄቨን እናት የመንግስት መኖሪያ ቤት አበርክቷል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ እና የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች ዛሬ የሄቨንን እናት በማግኘት አጽናንተዋል::
ልጇን በግፍ ተነጥቃ ባለፈው አንድ ዓመት ፍትሕ ሳታገኝ ለቆየችው ሲስተር አበቅየለሽ የፍትሕ ሒደቱን ለመከታተል ፣ያለችበት ሁኔታ የተሻለ እንዲሆንላትና ተጋላጭነቷን ለመቀነስ እንዲመች የከተማ አስተዳደሩ አንድ የመንግስት መኖሪያ ቤት አበርክቷል፡፡
ከዚህ ባለፈም በሙያዋ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ እንድትሰራ መመቻቸቱን ነው ከንቲባ አዳነች የገለጹት፡፡
የህጻን ሄቨን ጉዳይ የሁላችንም ጉዳይ በመሆኑ ድርጊቱ ተገቢውን ፍትሕ ማግኘቱ የሌሎች ህፃናት ተጋላጭነትን ለመቀነስ አስተዋጽኦ ያለው መሆኑን ከንቲባዋ አስገንዝበዋል፡፡
መሰል ጭካኔ የተሞላበት ድርጊት እንዳይፈፀም የማህበረሰቡ የአመለካከት ለውጥ እንዲመጣ እና ችግሩ የጋራ ጉዳይ በመሆኑ ሁሉም ሃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል፡፡