ለአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር 317 ሺህ 521 ሄክታር መሬት መዘጋጀቱ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የፊታችን ዓርብ ነሐሴ 17 ቀን 2016 ዓ.ም በሚከናወነው የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ሁሉም በነቂስ ወጥቶ እንዲሳተፍ ጥሪ ቀርቧል፡፡
የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) እና የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴዔታ ሰላማዊት ካሳ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በመግለጫቸውም÷የፊታችን ዓርብ ነሐሴ 17 ቀን ለሚከናወነው የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተካለ መርሐ-ግብር አስፈላጊው ዝግጅት መጠናቀቁን ገልጸዋል፡፡
ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)÷ለአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር በሁሉም ክልሎች 8 ሺህ 452 ካርታ የወጣላቸው ቦታዎች መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡
የተዘጋጁት ቦታዎች አጠቃላይ ስፋትም 317 ሺህ 521 ሄክታር መሆኑን ገልጸው÷ለተከላ የሚውሉ ችግኞች በቅርብ ሥፍራ ዝግጁ መደረጋቸውን አንስተዋል፡፡
የችግኝ ተከላ መርሐ ግብሩም ከማለዳው 12 ሰዓት ጀምሮ እስከ ምሽት 12 ሰዓት እንደሚከናወን ነው የገለጹት፡፡
በየአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባስተላለፉት መልዕክት መሰረት 600 ሚለየን ችግኝ ለመትከል ሁሉም ዜጋ በንቃት እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ሰላማዊት ካሳ በበኩላቸው÷የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የኢትዮጵያን የደን ሽፋን ከመጨመር ባለፈ ተጨባጭ የሆነ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ውጤት ማስገኘቱን አውስተዋል፡፡
በተጨማሪም ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የምታደርገውን ጥረት የሚያግዝና ለሌሎች ሀገራት አርአያ የሚሆን ተግባር መሆኑን ተናግዋል፡፡
በዕለቱ የችግኝ ተከላው የደረሰበትን ደረጃ በሚመለከት መረጃው በቴክኖሎጂ ታግዞ ለሕዝብ ተደራሽ እንደሚደረግ ተመላክቷል፡፡
በመላኩ ገድፍ