የዝንጀሮ ፈንጣጣ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ እየተሠራ ነው – ሚኒስቴሩ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 16፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ የቅድመ መከላከል ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ በሰጡት መግለጫ÷ የዝንጅሮ ፈንጣጣ በሽታ በዓለም የጤና ድርጅት የሕብረተሰብ ጤና ስጋት መሆኑ ከተገለፀ ጀምሮ በሽታው ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ የቅድመ መከላከል ሥራ እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
በዚሁ መሠረት÷ በድንበርና በተመረጡ አካባቢዎች ላይ ቅኝት የማድረግ፣ የልየታ ሥራ፣ በሽታውን መመርመር የሚያስችል የቤተ-ሙከራ አቅምን የማሳደግ እንዲሁም የባለሙያዎችን አቅም የማጎልበት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
የዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታ በ13 የአፍሪካ ሀገራት መከሰቱን በመግለጽ÷ እስካሁን በኢትዮጵያ በበሽታው የተያዘ ሰው አለመኖሩን ማረጋገጣቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡