ዘላቂ ልማት ለማረጋገጥ ለተፈጥሮ ሀብት ትኩረት መስጠት ይገባል- አቶ ጌታቸው ረዳ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በትግራይ ክልል ዘላቂ ልማት ለማረጋገጥ ለተፈጥሮ ሀብት ዘርፍ ትኩረት በመስጠት መሥራት እንደሚገባ የክልሉ ጊዜያዊ አሥተዳደር ርዕሰ መሥተዳድር ጌታቸው ረዳ አስገነዘቡ፡፡
በየደረጃው የሚገኙ የክልሉ አመራሮች፣ የሐይማኖት አባቶችና የተለያየዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች የተሳተፉበት በአንድ ጀምበር አረንጓዴ ዐሻራ የማኖር መርሐ-ግብር እየተከናወነ ነው፡፡
በዚሁ ወቅት አቶ ጌታቸው በእንደርታ ወረዳ አረንጓዴ ዐሻራቸውን ከአኖሩ በኋላ ባደረጉት ንግግር÷ ክልሉ በተፈጥሮ ሀብት ሥራዎች፣ ደንና አረንጓዴ ልማት በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና አግኝቶ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
ይሁን እንጂ ባለፉት ዓመታት በሰው ሠራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎች የተፈጥሮ ሀብት ልማት ሥራው ወደ ኋላ መመለሱን ጠቅሰዋል፡፡
በተፈጥሮ ሀብቱን ያጋጠመው መራቆት መልሶ እንዲያገግም እና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የአረንጓዴ ዐሻራ ሥራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል፡፡
#አረንጓዴዓሻራ
#600_ሚሊዮን_ችግኝ_በአንድ_ጀምበር
#የምትተክል_ሀገር፤ #የሚያፀና_ትውልድ