በሰሜን ጎንደር ዞን በተከሰተ የመሬት መንሸራተት አደጋ የ23 ሰዎች ሕይወት አለፈ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን በተከሰተ የመሬት መንሸራተት አደጋ የ23 ወገኖች ሕይወት ሲያልፍ ሥምንት ሰዎች የአካል ጉዳት ደረሰባቸው፡፡
አደጋው የተከሰተው በዞኑ በሚገኙ አራት ወረዳዎች በሚገኙ 11 የገጠር ቀበሌዎች መሆኑን የዞኑ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽሕፈት ቤት አስታውቋል፡፡
በመሬት መንሸራተት አደጋው የተጎዱ ወገኖችን ለመደገፍ ግብረ-ኃይል ተቋቁሞ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን የዞኑ ኮሙኒኬሽን መምሪያ መረጃ አመላክቷል፡፡
በአጠቃላይ በዞኑ በተከሰተው የመሬት መንሸራተት አደጋ የ23 ሰው ሕይወት ማለፉ፣ ከ2 ሺህ 700 በላይ ወገኖች ከቀያቸው መፈናቀላቸው፣ በ1 ሺህ 775 ሔክታር ላይ የተዘራ ሰብል መውደሙ፣ 48 መኖሪያ ቤቶች ላይ ጉዳት መድረሱ ተብራርቷል፡፡
ለተጎጂ ወገኖችም የዕለት ምግብን ጨምሮ የመጠለያ አገልግሎት እንዲያገኙ ግብረ-ኃይሉ ከየአካባቢዎቹ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጋር ተቀናጅቶ እየሠራ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡