Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ አየር መንገድን ደህንነት አደጋ ላይ ለመጣል ተንቀሳቅሰዋል ተብለው በሽብር ወንጀል የተጠረጠሩ 6 ግለሰቦች ፍ/ቤት ቀረቡ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ አየር መንገድን ደህንነት አደጋ ላይ ለመጣል ተንቀሳቅሰዋል ተብለው በሽብር ወንጀል የተጠረጠሩ 6 ግለሰቦች ፍርድ ቤት ቀረቡ፡፡

የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት ዛሬ ከሰዓት በኋላ በተጠርጣሪ ዮሃንስ ዳንኤል በርሄ (ጆን ዳንኤል)፣ አማኑኤል መውጫ አብርሃ፣ ናትናኤል ወንድወሰን ሹሜ፣ ኤልያስ ድሪባ በዳኔ፣ ይዲድያ ነጻነት አበበ እና እሌኒ ክንፈ ተክለአብ በተባሉ ግለሰቦች ላይ ፖሊስ ያቀረበውን የጥርጣሬ መነሻና የተጠርጣሪ ጠበቆቻቸውን መከራከሪያ ነጥብ ተመልክቷል፡፡

ተጠርጣሪዎችን ፍርድ ቤት ያቀረበው የፌደራል ፖሊስ መርማሪ ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹ በነሐሴ 16 ቀን 2016 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ወደ መቀሌ ለጉዞ በተዘጋጀ አውሮፕላን ውስጥ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሲቪል አቪዬሽን ሕግና አሰራር በመጣስ፣ የአየር መንገዱን ደህንነት አደጋ ላይ ለመጣል፣ የደህንነት ባለሙያዎችን በተንቀሳቃሽ ምስል በመቅረጽ የአየር መንገዱ ላይ ጥቃት ለማድረስ ሲንቀሳቀሱ እንደነበር ጠቅሶ የጥርጣሬ መነሻውን ለጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ አብራርቷል።

“ክረምቱን ተከትሎ ከተከሰተው የአየር መዛባት ሁኔታ ጋር ተያይዞ አውሮፕላኑ መብረር እንደማይችል የገለጹ የበረራ ባለሞያዎችን በማስገደድና አንወርድም በማለት ለ2 ሰዓታት አውሮፕላኑን በማገት አመጽ ለማስነሳት ግርግር ፈጥረዋል” በማለት መርማሪ ፖሊሶች የጥርጣሬ መነሻቸውን ለጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ አስረድቷል።

በተጨማሪም ተጠርጣሪዎቹ ከጸረ-ሰላም ሃይሎች ተልዕኮ ተቀብለው የሀገሪቱን አየር መንገድ ገጽታ ለማበላሸትና የደህንነት ሥራን ለማስተጓጎልና ጥቃት ለማድረስ የተንቀሳቀሱ መሆናቸውን መርማሪ ጠቅሶ ምርመራውን በስፋት ለማከናወን የ14 ቀን ጊዜ ቀጠሮ እንዲሰጠው ችሎቱን ጠይቋል።

የተጠርጣሪ ጠበቆች በበኩላቸው÷ደንበኞቻቸው በዕለቱ ለጉዞ ወደ መቀሌ ለመሄድ በተዘጋጁበት ወቅት በረራው በመዝግየቱ ተበሳጭተው የተፈጠረ አለመግባባት እንጂ የሽብር ተልኮ ይዘው “አይደለም “በማለት የመከራከሪያ ነጥባቸውን አቅርበዋል።

ጠበቆቻቸው”በፖሊስ የቀረበው የጥርጣሬ መነሻ የሽብር ተግባሩን የማያሟላ እና የፍሕ ፖሊስንና የወንጀል መርሕን ያልተከተለ ነው “በማለት የመከራከሪያ ነጥብ አቅርበዋል።

“ከአንደኛው ተጠርጣሪ በስተቀር በማህበራዊ ሚዲያ በቀጥታ እየቀረጸ ያስተላለፈ የለም ያሉ ሲሆን÷የሌሎች ተጠርጣሪዎች ተሳትፎ ተለይቶ ሳይገለጽ ፣በጋራ ለሽብር ጥቃት ተንቀሳቅሰዋል ተብሎ መቅረቡ ተገቢ አይደለም በማለትም” ተከራከረዋል።

ነሐሴ 18 ቀን 2016 ዓ.ም በመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት አራዳ ምድብ በተመሳሳይ ጥያቄ ቀርበው በ20 ሺህ ብር ዋስ ተፈቅዶላቸው እንደነበር ጠቅሰው÷በድጋሚ ከፍተኛ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ መደረጉ አግባብ አይደለም በማለት መዝገቡ እንዲዘጋላቸው፤ ይህ ከታለፈ ደግሞ ዋስትና እንዲፈቀድላቸው ጠይቀዋል።

6ኛ ተጠርጣሪን በሚመለከት “ልጆች ተሸክሜ በአየር መንገዱ ተንገላትቻለው ብለሻል”ተብላ በፖሊስ የተያዘች እንጂ ተጠርጣሪዋ ልጆች የሌላትና ከዚህ በፊት በአየር መንገዱ ውስጥ ትሰራ የነበረች እንደሆነች ጠበቃዋ ጠቅሶ የወንጀል ተሳትፎ የላትም የሚል ክርክር አንስቷል፡፡

በጊዜ ቀጠሮ መዝገቡን በሚመለከቱት ዳኛ 6ኛ ተጠርጣሪ “3 ልጀች ይዤ ተንገላታሁ በማለቷ በስህተት ነው የተያዘች “ለሚለው የጠበቃ መከራከሪያ ላይ ፖሊስ ማብራሪያ እንዲሰጥበት ጠይቀዋል፡፡

በዚህም መርማሪ ፖሊስ ተጠርጣሪዋ በስህተት ሳይሆን አውሮፕላን በማገትና ጥቃት በማድረስ ወንጀል ተሳትፎ ያላት በመሆኗ ነው የተያዘችው በማለት ማብራሪያ ሰጥቷል።

በሌላ በኩል የችሎቱ ዳኛ ከዚህ በፊት ቅዳሜ ዕለት በተመሳሳይ ጥያቄ በመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት መቅረባቸውንና አለመቅረባቸውን እንዲሁም ዋስትና መሰጠቱንና አለመሰጠቱን የማረጋገጫ ጥያቄ ለፖሊስ ያቀረቡ ሲሆን÷መርማሪ ፖሊስ የሽብር ወንጀሎችን የመመርመር ስልጣን ያለው የፌዴራል ፖሊስ መሆኑን ጠቅሶ በእኛ በኩል ከዚህ በፊት በመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት አላቀረብናቸውም ሲል መልስ ሰጥቷል።

በተጠርጣሪ ጠበቆች በኩል በአጋጣሚ ተበሳጭተው የተፈጠረ እንጂ የሽብር ተግባር የላቸውም በማለት ላነሱት መከራከሪያ ነጥብ መልስ የሰጠው መርማሪ ፖሊስ ከፀረ ሰላም ሃይል የተሰጣቸውን ተልዕኮ ተቀብለው ሆን ብለው የአየር መንገዱን ስም በማጠልሸት፣ በአየር መንገዱ ደህንነት ላይ አደጋ ለመጣልና ጥቃት ለማድረስ የተንቀሳቀሱ መሆናቸውን ጠቅሶ÷መርማሪ ፖሊስ በጠበቆች መከራከሪያ ነጥብ ላይ መልስ ሰጥቶ አብራርቷል።

በተጨማሪም መርማሪ ፖሊስ ተጠርጣሪ ሪዎቹ “ከዚህ በፊት የጦር መሳሪያና የፀጥታ አካላት ልብስ ለብሰው የተነሱት ፎቶና ሌሎች ጠቋሚ ማስረጃዎች ማግኘቱን ጠቅሶ ይህን መነሻ በማድረግ ሰፋ ያለ ምርመራ ማጣሪያ እንደሚያከናውን አመልክቷል፡፡
ስለሆነም ከወንጀሉ ድርጊቱ አደገኝነትና ውስብስብነት አንጻር ተጠርጣሪዎቹ ያላቸውን ተከታይ ተጠቅመው ተጽዕኖ ሊፈጥሩ ይችላሉ “በማለት ዋስትና ጥያቄያቸው ውድቅ ተደርጎ የጠየቀው የምርመራ ማጣሪያ ጊዜ እንዲፈቀድለት ጊዜ ቀጠሮ ችሎቱን ጠይቋል።

የግራ ቀኝ ክርክሩን የመረመረው ችሎቱ ቅዳሜ ዕለት በተመሳሳይ ጥያቄ በመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ስለመቅረባቸውና ዋስትና ስለመሰጠቱ ከጠበቆች ማረጋገጫ እንዲያቀርብ በማለት እንዲሁም ምርመራው ማጣሪያ መዝገቡ በይደር 3 ሰዓት እንዲቀርብ በማለት መርምሮ ተገቢውን ትዕዛዝ ለመስጠት ለነገ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.