ምክር ቤቱ ነገ መደበኛ ስብሰባውን ያደርጋል
አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 17፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን 17ኛ መደበኛ ስብሰባ ነገ በጠቅላይ ሚኒስቴር ፅህፈት ቤት ይካሄዳል።
በነገው ስብሰባም የምክር ቤቱን 5ኛ አመት የስራ ዘመን 16ኛ መደበኛ ስብሰባ ቃለ ጉባኤ እንዲሁም የተጓደሉ የእርቀ ሰላም ኮሚሽን አባላት ሹመትን መርምሮ ያጸድቃል።
በተጨማሪም የንግድና ኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ለመመደብ የቀረበ የውሳኔ ሃሳብን፣ የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የአፍሪካ ሕብረት ሰንደቅ ዓላማ፣ መዝሙር እና የአፍሪካ ቀን ረቂቅ አዋጅ በተመለከተ ያቀረበውን ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብ መርምሮ ረቂቅ አዋጁን እንደሚያጸድቅም ይጠበቃል።
እንዲሁም የገቢ፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እና የከተማ ልማት፣ ኮንስትራክሽን እና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የፌደራል መንግስት ፕሮጀክቶች አስተዳደር እና አመራር ስርዓትን ለመደንገግ የቀረበ ረቂቅ አዋጅን በተመለከተ የቀረበን ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብ መርምሮ ያጸድቃልም ነው የተባለው።
በተጨማሪም የገቢ፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የልዩ የመንግስት ዕዳ ሰነድ ረቂቅ አዋጅን በተመለከተ ያቀረበውን ሪፖርት ጨምሮ በ15 አጀንዳዎች ላይ በመወያየት ያጸድቃል መባሉን ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።