10 ሺህ የዝንጀሮ ፈንጣጣ መከላከያ ክትባት ናይጄሪያ ደረሰ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) 10 ሺህ የዝንጀሮ ፈንጣጣ መከላከያ ክትባት ናይጄሪያ ደረሰ።
የዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታ የዓለም የጤና ስጋት መሆኑ ከተገለጸ ወዲህ ክትባቱን በመረከብ ናይጄሪያ የመጀመሪያዋ አፍሪካዊት ሀገር መሆኗ ተገልጿል።
በዓለም የጤና ድርጅት የዓለም የጤና ስጋት ብሎ የለየው የዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታ መከላከያ ክትባት በአፍሪካ በበቂ ሁኔታ እየተዳረሰ እንዳልሆነ ተነግሯል።
በሽታውን ለመከላከል 10 ሺህ ክትባት የተረከበችው ናይጄሪያ፤ በሽታው በወረርሽኝ መልክ ከተከሰተ ወዲህ ከፍተኛውን የክትባት ያገኘች የመጀመሪያዋ አፍሪካዊት ሀገር ሆናለች።
በሀገሪቱ እስካሁን 40 ያህል ሰዎች በበሽታው የተያዙ ቢሆንም በዚህ ምክንያት ያጋጠመ ሞት አለመኖሩ ተገልጿል።
ናይጄሪያ የተረከበችውን ክትባት ቅድሚ ለጤና ባለሙያዎች በመስጠት ተደራሽ የምታደርግ መሆኗ ተመላክቷል።
የመካከለኛ አፍሪካዋ ዲሞክራቲክ ኮንጎ በቫይረሱ ክፉኛ ከተጎዱ ሀገሮች መካከል ግንባር ቀደም ስትሆን 18 ሺህ ሰዎች በበሽታው ሲጠቁ 615 ሰዎች በበሽታው ምክንያት ህይወታቸውን እንዳጡ ቢቢሲ ዘግቧል።
የአለም ጤና ድርጅት እንዲሁም የአፍሪክ በሽታዎች መከላከል እና መቆጣጠር ማዕከል አማካሪ ፕሮፌሰር ሄለን ሪስ የአለም የጤና ዘርፍ አካላት ለጉዳዩ በቂ ትኩረት እንዲሰጡ አሳስበዋል፡፡
የመድሃኒት አምራች እና አቅራቢ ድርጅቶችም የዝንጀሮ ፈንጣጣ መከላከያ ክትባትን በስፋት በማቅረብ ሂደት ትብብር እንዲያደረጉ ጥሪ አስተላልፈዋል።
የዝንጀሮ ፈንጣጣ ቫይረስ በዴንማርክ (በፈረንጆቹ 1958) በዝንጀሮዎች ውስጥ የተገኘ ሲሆን ለመጀመሪያ ጊዜ በሰው ልጅ ላይ የተገኘው በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ነው፡፡