የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንትን ጨምሮ በ18 ተጠርጣሪዎች ላይ ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ ተመሰረተ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት የነበሩት ሀብታሙ አበበ (ዶ/ር) ጨምሮ በ18 ተጠርጣሪዎች ላይ ተደራራቢ ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ ተመሰረተባቸው።
በፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ ዛሬ በፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ ተረኛ ወንጀል ችሎት ክስ መስርቷል።
ክስ የተመሰረተባቸው 1ኛ በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት በነበሩት ሀብታሙ አበበ ( ዶ/ር)፣ 2ኛ በዩኒቨርሲቲው ም/ፕሬዚዳንት በነበሩት ታምራት ታገሰ (ዶ/ር)፣ 3ኛ የዩኒቨርሲቲው የግንባታ ጽ/ቤት ኃላፊ ኢንጂነር ሙላቱ ኤርቲሮ፣4ኛ በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የፋይናንስ ዳይሬክተር ማርቆስ ዮሐንስ፣ 5ኛ በዩኒቨርሲቲው የፋይናንስ ዳይሬክቶሬት የውስጥ ገቢ የቡድን መሪ ደስታ ደቦጭ፣ 6ኛ የዩኒቨርሲቲው የፋይናንስ ዳይሬክቶሬት ቡድን መሪ መሰረት ለማ፣ 7ኛ በዩኒቨርሲቲው ጠቅላላ አገልግሎት ኃላፊ ወ/ሮ ደብሪቱ ተስፋዬ መንገሻን እና ሁለት የግል ድርጅቶችን ጨምሮ አጠቃላይ 18 ተከሳሾች ናቸው።
በዚህም በቀረበው 1ኛ ክስ ላይ በ1ኛ፣ 8ኛ እና 15ኛ ተከሳሾች ላይ ብቻ የቀረበ ሲሆን ይኸውም በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ህግ አንቀፅ 33 እና 34 እንዲሁም የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀፅ 5 እና አንቀፅ 9 ንዑስ ቁጥር 1 (ሀ) እና ንዑስ ቁጥር 2 (ሀ) ላይ የተመለከተውን መተላለፍ የሚል ክስ ይጠቀሳል።
በዚህም 1ኛ ተከሳሽ በዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንትነት ሆኖ ሲሰራ የማይገባ ጥቅም ለራሱ ለማግኘት በወንጀል ድርጊቱ ልዩ ተካፋይ ናቸው ለተባሉት 8ኛ እና 15ኛ ተከሳሾችም ለማስገኘት በማሰብ፣ ተከሳሾች እርስ በእርስ በጥቅም በመመሳጠርና የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር አዋጅ እና የፌደራል መንግስት የግዥ አፈጻጸም መመሪያን በመተላለፍ 8ኛ ተከሳሽ በባለቤትነት ከሚያስተዳድረው ኤ.ኤ.ኤም.ኢ.ዲ ቴክኖሎጂስ ኢንካ ከተባለው ከ15ኛ ተከሳሽ በዩኒቨርሲቲው ለንግስት እሌኒ መሐመድ መታሰቢያ ሆስፒታል የኦክሲጂን ማምረቻ ግዥ እንዲፈጸም በማድረግ ለ5 ዓመት የመለዋወጫ ዕቃ አቅርቦት፣ ጥገና እና እድሳት አገልግሎት በጠቅላላው 22 ሚሊየን 148 ሺህ 428 የአሜሪካ ዶላር በሕዳር 29 ቀን 2013 ዓ.ም በዩኒቨርሲቲው በኩልና በድርጅቱ በኩል 1ኛ እና 8ኛ ተከሳሽ በመሆን መፈራረማቸው በክሱ ተጠቅሷል።
1ኛ ተከሳሽ በሀምሌ 22 ቀን 2013 ዓ.ም የተሰራው ጠቅላላ ሥራ 25 ከመቶ ብቻ ሆኖ እያለ ሙሉ ክፍያ በወቅቱ በነበረው የኢትዮጵያ ብር የውጪ ምንዛሬ ተመን 1 ቢሊየን 55 ሚሊየን 618 ሺህ 286 ብር ከ26 ሳንቲም ለድርጅቱ እንዲከፈል በማድረግ፣ 8ኛ እና 15ኛ ተከሳሾችም ስራውን ጨርሰው ባላስረከቡበት ሁኔታ ላይ ምንም አይነት ስራ ባልተሰራበት ሁኔታ ለጥገናና እድሳት በሚል የተያዘውን ክፍያ በመቀበል በህገወጥ መንገድ ጥቅም ያገኙና በዚህ ልክ በመንግስት ላይ ጉዳት እንዲደርስ “አድርገዋል” በማለት ዐቃቤ ሕግ በክሱ ላይ በዝርዝር አስፍሯል።
በዚህ መልኩ ስራው በውል ጊዜው ባለመጠናቀቁ ወደ ዩኒቨርሲቲው ሂሳብ ገቢ መሆን የነበረበትን የመልካም ስራ አፈጻጸም ዋስትና ገንዘብ 2 ሚሊየን 214 ሺህ 852 የአሜሪካ ዶላር 15ኛ ተከሳሽ ማቅረብ ሲገባው ባለማቅረቡ 1ኛ ተከሳሽም ይህንን ተከታትሎ የሚያስፈጽም ውል አስተዳደሪ ባለመመደቡ ለመንግስት ገቢ ሳይደረግ በመቅረቱ በዚሁ ልክ በመንግስት ላይ ጉዳት እንዲደርስ በማድረጉና 8ኛ እና 15ኛ ተከሳሾች ለ1ኛ ተከሳሽ 9 ሚሊየን ብር መስጠታቸው ተጠቅሶ በአጠቃላይ 1ኛ ተከሳሽ በዋና ወንጀል አድራጊነት 8ኛ እና 15ኛ ተከሳሾች ደግሞ በልዩ ወንጀል ፈጻሚነት ተካፋይ በመሆን በፈጸሙት ስልጣንን ያለአግባብ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል ተከሰዋል የሚል ይገኝበታል።
በ2ኛ ክስ ደግሞ በ1ኛ፣ 2ኛ፣ 3ኛ እና 9ኛ ተከሳሾች ላይ እንደተመላከተው 1ኛ፣2ኛ እና 3ኛ ተከሳሾች በዩኒቨርሲቲው በፕሬዚዳንትነት፣ በአካዳሚክና ምርምር ምክትል ፕሬዚዳንትነት፣ የፕሮጀክት ጽ/ቤት ኃላፊነት ተመድበው ሲሰሩ 9ኛ ተከሳሽ ደግሞ በግንባታ ስራ ላይ ተሰማርቶ እያለ በልዩ ወንጀል ተካፋይ በመሆን በተለይም በተገባ ውል ከሚሰራው የ276 ሚሊየን 657 ሺህ 616 ብር ከ38 ሳንቲም በልዩነት ብልጫ እንዲኖረው በማድረግ 9ኛ ተከሳሽ የማይገባ ጥቅም እንዲያገኝ እና በዚያው ልክ በመንግስት ላይ ጉዳት እንዲደርስ ያደረጉ መሆኑ ተጠቅሶ በክሱ ላይ 1ኛ፣ 2ኛ፣ 3ኛ ተከሳሽ በዋና ወንጀል አድራጊነት 9ኛ ተከሳሽ ደግሞ ልዩ የወንጀል ድርጊት ተካፋይ በመሆን ስልጣንን ያለአግባብ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል ተከሰዋል
3ኛ ክስ ደግሞ በ1ኛ፣ 2ኛ፣ 3ኛ እና 9ኛ ተከሳሾ ላይ ብቻ የቀረበ ሲሆን ይኸውም 1ኛ፣2ኛ እና 3ኛ ተከሳሾች 9ኛ ተከሳሽ ያቀረበው የውል ማስከበሪያ 36 ሚሊየን 768 ሺህ 881 ብር ከ86 ሳንቲም ለመንግስት ገቢ እንዲደረግ ለዩኒቨርሲቲው የፋይናንስ ወይም ግዥ ዳይሬክቶሬት ማሳወቅ ሲገባቸው ይህንን ባለማድረጋቸው በመንግስት ላይ በዚሁ ልክ ጉዳት እንዲደርስ ያደረጉ እና 9ኛ ተከሳሽ ጥቅም እንዲያገኝ በማድረግ በዋና ወንጀል አድራጊነትና በልዩ ወንጀል ፈጻሚነት ተካፋይ በመሆን ስልጣንን ያለአግባብ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል ተከሰዋል።
በ4ኛ ክስ ደግሞ በ1ኛ፣ 5ኛ፣ 6ኛ እና 7ኛ ተከሳሾች ላይ ብቻ የቀረበ ሲሆን በዩኒቨርሲቲው ሲሰሩ ከዩኒቨርሲቲው ሂሳብ በተለያየ መጠን 6 ሚሊየን 130 ሺህ 398 ብር ከ07 ሳንቲም ወደ ራሳቸው ሂሳብ ቁጥር በማስተላለፍ ለግል ጥቅማቸው በማዋል እና በዚህ ልክ ጉዳት እንዲደርስ ያደረጉ መሆናቸውን ተጠቅሶ በዋና ወንጀል አድራጊነትና ተካፋይ በመሆን ስልጣንን ያለአግባብ መገልግል ከባድ የሙስና ወንጀል ተከሰዋል፡፡
በሌላኛው በ8ኛ ክስ ደግሞ በ7ኛ፣ 9ኛ፣ 11ኛ፣ 12ኛ፣ 13ኛ፣ 14ኛ፣ 15ኛ እና 17ኛ ተከሳሾች ላይ ብቻ የቀረበ ሲሆን ይኸውም በሙስና ወንጀል የተገኘ 9 ሚሊየን ብር በተለያዩ መጠኖች ምንጩን በመደበቅ ወይም ህጋዊ በማስመሰል ይዘው የተገኙ፣ ለሎሎች ሰዎች ያዘዋወሩ/ያስተላለፉ መሆናቸው ተጠቅሶ በዋና እና በልዩ ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በወንጀል ድርጊት የተገኘን ገንዘብ ወይም ንብረትን ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ ወንጀል ተከሰዋል፡፡
በዚህ መልኩ ዐቃቢህግ በየተሳትፎ ደረጃ ጠቅሶ አጠቃላይ 8 ከሶችን በየደረጃው አቅርቧል።
ክሱ ከቀረበባቸው መካከል 1ኛ፣ 2ኛ፣ 3ኛ፣ 4ኛ፣ 9ኛ እና 17ኛ በተረኛ ችሎት ቀርበው የክስ ዝርዝሩ እንዲደርሳቸው እና በንባብ ዝርዝሩን እንዲሰሙ ተደርጓል።
ከተከሳሾቹ መካከል ዋስትና በማያስከለክል ድንጋጌ ማለትም በህገ ወጥ መንገድ የተገኘ ንብረትን ወይም ገንዘብን ምንጩን ደብቆ ህጋዊ አድርጎ ማቅረብ ወንጀል የተከሰሱት 17ኛ ተከሳሽ በ30 ሺህ ብር ዋስትና የተፈቀደላቸው ሲሆን ሌሎቹ ግን የተከሰሱበት ክስ ዋስትና ስለሚያስከለክል በማረሚያ ቤት ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ በማለት የክስ መቃወሚያ ካላቸው ለመጠባበቅ ለጥቅምት 17 ቀን 2017 ዓ.ም ተቀጥሯል።
በታሪክ አዱኛ