ኢፋድ የኢትዮጵያ የገጠር ልማት ስራዎችን መደገፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ዓለም አቀፉ የግብርና ልማት ፈንድ (ኢፋድ) የኢትዮጵያ መንግስትን የገጠር ልማት ስራዎች መደገፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀ።
የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ ከኢፋድ ተባባሪ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶናል ብራውን ጋር ተወያይተዋል።
በውይይታቸውም ኢፋድ እየሰጠው ስላለው ድጋፍ እና በቀጣይ ትብብር ዙሪያ መክረዋል።
አቶ አህመድ ሺዴ ኢትዮጵያ እያካሄደችው ስላለው የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም፣ በምግብና ስነ ምግብ ትራንስፎርሜሽን አጀንዳ የገጠር ኑሮን ለማሻሻል እንዲሁም የምግብ ዋጋ ንረትን ለማረጋጋት እየተካሄዱ ስላሉ ተግባሮች ገለጻ አድርገዋል።
ሚስተር ዶናል ብራውን በበኩላቸው የኢትዮጵያ መንግስት በገጠር የጀመራቸውን የልማት ስራዎች ኢፋድ እየደገፈ መሆኑን ጠቅሰው፤ ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
ኢፋድ በኢትዮጵያ ውስጥ የአርሶ እና አርብቶ አደሮችን ምርታማነትንና አቅም የሚያሳድጉ አራት ፕሮጀክቶችን በ320 ሚሊየን ዶላር እየደገፈ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል።