ቢሮው የሻደይ፣ አሸንድዬ እና ሶለል በዓላትን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ለማሳደግ እንደሚሠራ ገለጸ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሻደይ፣ አሸንድዬ እና ሶለል በዓላት እሴታቸው ተጠብቆ ጎብኚዎችን በመሳብ የሚያስገኙትን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማሳደግ እንደሚሠራ የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ፡፡
ከነሐሴ አጋማሽ ጀምሮ በአማራ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች ሲከበሩ የቆዩት ሻደይ፣ አሸንድዬ፣ ሶለል፣ ቡሄና እንግጫ ነቀላ በዓላት የማጠቃለያ መርሐ-ግብር ዛሬ በባሕር ዳር ከተማ ተካሂዷል።
የባሕልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር÷ በዓላቱ እሴታቸው ተጠብቆ ማኅበራዊ ትስስርን በማሳደግ የኢኮኖሚያ ጠቀሜታ እንዲያስገኙ መሥራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ እነዚህ በዓላት የወልነት ባሕሪ ያላቸውና በአንድነት በመሰባሰብ የሚከበሩ እንደመሆናቸው ሕዝብን ከሕዝብ የሚያስተሳስሩ ናቸው ብለዋል፡፡
በዓላቱ ስማቸውን እየቀያየሩም ቢሆን በአማራ ክልል በሁሉም አካባቢዎች ከክረምቱ መውጣትና ከልምላሜ ወራት መገለጫነት ጋር የሚከበሩ መሆናቸው የሕዝባችንን የባህል አንድነት ያሳያል ሲሉም ገልጸዋል፡፡
የሻደይ፣ አሸንድዬ፣ ሶለል፣ ቡሄ እና እንግጫ ነቀላ በዓላት ባሕላዊ አከባበራቸውና እሴታቸው ተጠብቆ ጎብኚዎችን በመሳብ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን እንዲያሳድጉ በትኩረት ይሠራል ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ መልካሙ ጸጋዬ ናቸው፡፡
በደሳለኝ ቢራራ