Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ ፌዴራሊስት ኃይሎች ጥምረት ህወሓትን ከጥምረቱ አባልነት ሰረዘ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 18፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ)የኢትዮጵያ ፌዴራሊስት ኃይሎች ጥምረት ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) እና የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሕብረት (ኢዴሕ)ን ከጥምረቱ መተዳደሪያ ደንብ ውጪ ሆነው ተገኝተዋል በሚል ከአባልነት መሰረዙን አስታወቀ።

ጥምረቱ አራተኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን በአዲስ አበባ አካሄዷል።

በዚሁ ጊዜ ጥምረቱ በአደረጃጀቱ ላይ ሰፋ ያለ ውይይት ያደረገ ሲሆን፤ የአገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታና የጥምረቱ ቀጣይ አቅጣጫ ላይም ተወያይቷል።

ጥምረቱ በአደረጃጀቱ ላይ ውይይት ሲያደርግ ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ጥምረቱ ውስጥ ወዥንብር እየፈጠረ ነው ብለዋል።

የጥምረቱ የአደረጃጀት ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ቶሎሳ ተስፋዬ “ፓርቲው የጥምረቱ አባላትን ለመከፋፈል የተለያዩ ጫናዎች እየፈጠረ ነው” ይላሉ።

“ይህ ብቻ ሳይሆን ህወሓት ጥምረቱን እንደ ሽፋን ተጠቅሞ አገርን ለማወክ እየተንቀሳቀሰ ነው” ሲሉም ገልጸዋል።

በተጨማሪም ፓርቲው በጥምረቱ ሰብሰባ ላይ እንደማይገኝና የጥምረቱ ስብሰባም መቀሌ ካልተካሄደ ተቀባይነት እንደሌለው እየገለጸ ነው ሲሉ ከስሰዋል።

አቶ ቶሎሳ “ህወሓት እኔ ያልኩት ካልሆነና እኛ ካልመራን ትክክል አይደለም የሚል” ግትር አቋም ያራምዳል ሲሉም ክሳቸውን ያቀርባሉ።

ህወሓት በቀጣይ ከጥምረቱ ጋር ‘ይቀጥል ወይስ ይሰረዝ’ በሚለው ጉዳይ ላይ የጥምረቱ አባላት ሰፋ ያለ ውይይት አድርገዋል።

በውይይቱ የተወሰኑ አባላት ህወሓትን ጨምሮ ሌሎች መተዳደሪያ ደንቡን የማያከብሩ ከጥምረቱ ይሰረዙ ሲሉ፣ በቁጥር በርከት ያሉት ደግሞ ‘አንድ ዕድል’ ይሰጣቸው ብለዋል።

በመጨረሻም ጥምረቱ ህወሓት በቀጣዩ ጉባኤ እንዲሳተፍ ጥሪ ተደርጎ አቋሙን ግልጽ ያድርግ በማለት ውሳኔ አሳልፎ ነበር።

ይሁንና የጥምረቱ አመራሮች ከጉባኤው በኋላ በኢዜአ ተገኝተው በጉባኤው የተደረሰበትን የውሳኔ ሀሳብ አሳውቀዋል።

የጥምረቱ ሊቀ-መንበር አቶ ደረጄ በቀለ እንደሚሉት ህወሓትና ኢዴሕ ሕገ ወጥ በሆነ መልኩ እየተንቀሳቀሱ በመሆኑ ታግደዋል፤ ይህንንም ሁሉም የጥምረቱ አባላት የተስማሙበት ጉዳይ ነው ይላሉ።

በጉባኤው ወቅት ተገኝቶ መታዘብ እንደቻለው በጉዳዩ ላይ አባላቱ ለሁለት ተከፍለው ክርክር ተደርጎ፤ ይፋዊ የድምጽ አሰጣጥ ተካሂዶ ለፓርቲዎቹ አንድ ተጨማሪ እድል እንዲሰጠው ተስማምተው ነበር።

አቶ ደረጄ ”ሁሉም የጥምረቱ አባላት በሁለቱ ፓርቲዎች መሰረዝ ላይ ስምምነት ላይ ደርሰዋል” በማለት ከጉባኤው በኋላ የደረሱበትን ስምምነት ገልጸዋል።

ጥምረቱ እዚህ ዉሳኔ ላይ ከመድረሱ በፊት ምን አድርጓል የሚል ለቀረበው ጥያቄ “ጥምረቱ ግንቦት 6 ባካሄደው ስብስባ ፓርቲዎቹ ቀጥሎ በሚካሄደው ጉባኤ ላይ ካልተሳተፉ እንደሚታገዱ ተገልጾላቸው ነበር” ብለዋል።

ከዚያ በኋላም ሶስት ጊዜ በስልክ ፓርቲዎቹ ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶ እንደነበረ አስታውሰዋል።

“ለፓርቲዎቹም በነገው ዕለት መታገዳቸውን የሚገልጽ ደብዳቤ ይጽፋል” ሲሉም ገልፀዋል።

ሊቀመንበሩ “በተለይ ህወሓት 6ኛው ብሔራዊ ምርጫ ተራዝሞ ሳለ ለጥምረቱ ሳያሳውቅ ምርጫ አካሂዳለሁ ማለቱ የህገ ወጥነቱ ማሳያ ነው” ብለዋል።

ጥምረቱ 24 ፓርቲዎችን ያቀፈ ሲሆን በትናንቱ ጉባኤው 22 የፖለቲካ ፓርቲዎች ተገኝተዋል፤ ሌሎች አምስት የፖለቲካ ፓርቲዎች ደግሞ ጥምረቱን መቀላቀላቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.