ዓለምአቀፋዊ ዜና

የመን በቂ የፋይናንስ ድጋፍ ባለማግኘቷ የከፋ ችግር ገጥሟታል – ተመድ

By Meseret Awoke

June 25, 2020

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 18፣ 2012(ኤፍ ቢ ሲ) የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ጉዳይ ሀላፊ የመን በቂ የሆነ የፋይናንስ ድጋፍ ባለማግኘቷ ሳቢያ የከፋ ችግር ተጋርጦባታል ሲሉ አስጠነቀቁ፡፡

ሃላፊው ማርክ ሎውኮክ በርካታ የየመን ዜጎች በረሃብ ሳቢያ ፤ አሁን ላይ በየጊዜው ስጋቱ እየጨመረ ባለው የኮሮና ቫይረስ እንዲሁም በኮሌራ ይሞታሉ ብለዋል።

ህጻናቱም ክትባት ስላልወሰዱ በገዳይ በሽታዎች ሳቢያ እንደሚሞቱ ትናነት በዝግ በተካሄደው የፀጥታ ምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ ገልጸዋል፡፡

በየመን ኮሮናቫይረስ በፍጥነት እየተሰራጨ መሆኑን ጠቅሰው በአገሪቱ በቫይረሱ ከተያዙት መካከል 25 ከመቶ የሚሆኑት ህይወታቸው ማለፉን ጠቅሰዋል ፡፡

ከጤና ስርዓቱ ጋር በተያያዘ በአብዛኞቹ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች እንዲሁም ህይወታቸው ያለፉ ሰዎች ቁጥጥር እንዳልተደረገበት ጨምረው ገልጸዋል፡፡

በሁለት ሳምንታት ብቻ የየመን ምንዛሬ ሲያሽቆለቁል የምግብ ዋጋም ከ10 ወደ 20 በመቶ ማሻቀቡም ነው የተነገረው፡፡

ምንጭ፦ አልጀዚራ