የከተማ አስተዳደሩ በተለያዩ ክልሎች ለሚገኙ የመንግስት ሰራተኞች የጋራ መኖሪያ ቤቶችን እየሰጠ ነው በሚል እየተሰራጨ ያለው መረጃ ፍፁም ከእውነት የራቀ መሆኑን ገለፀ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 18፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተለያዩ ክልሎች ለሚገኙ የመንግስት ሰራተኞች የጋራ መኖሪያ ቤቶችን እየሰጠ ነው በሚል እየተሰራጨ ያለው መረጃ ፍፁም ከእውነት የራቀ መሆኑን ገለፀ።
የከተማ አስተዳደሩ እያስገነባቸው የሚገኙ የጋራ መኖሪያ ቤቶች በህጋዊ መንገድ ተመዝግበው ለሚገኙ ነዋሪዎች እንጂ ለተለያዩ ክልል ሰራተኞችም ይሁን ግለሰቦች የሚሰጥበት አሰራር የለውም ብሏል የከንቲባ ጽህፈት ቤት ባወጣው መግለጫ።
በ13ኛው ዙር እጣ የወጣላቸውና የወሰን ችግር የሌለባቸው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ለነዋሪዎች እየተላለፉ መሆኑን በመግለጫው ተመላክቷል።
ከትናንት በስትያ ጀምሮ የቁልፍ ርክክብ እየተካያሄደ መሆኑንና በሁለት ሳምንት ውስጥም የቁልፍ ርክክብ የሚጠናቀቅ ይሆናል ብሏል።
“ከዚህ ውጪ በየትኛውም መንገድ የእጣ ማውጣት ሂደት የተከናወነ አለመሆኑን ለማሳወቅ እንወዳለን” ብሏል የከተማ አስተዳደሩ።
“የከተማ አስተዳደሩ በተለያዩ ክልሎች ለሚገኙ የመንግስት ሰራተኞች የጋራ መኖሪያ ቤቶችን እየሰጠ ነው” በሚል እየተሰራጨ ያለው መረጃ ፍፁም ከእውነት የራቀ መሆኑንም አስታውቋል።
የዚህ አይነቱ ፍፁም የሀሰት መረጃዎች የከተማ አስተዳደሩን በተለይ በግዙፍ ፕሮጀክቶች አፈፃፀም ላይ እያሳየ ያለውን እመርታ ለማጠልሸትና ጥርጣሬ ለመፍጠር እንደሆነ እንደሚረዳም ገልጿል።
“በመሆኑም ህብረተሰባችን ይህንን ተረድቶ ራሱን ከሀሰት መረጃዎች እንዲያርቅ አደራ ለማለት እንወዳለን” ብሏል የከተማ አስተዳደሩ ባወጣው መግለጫ።
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።