ጀርመን ለመልሶ ማቋቋም ተጨማሪ የ4 ሚሊየን ዩሮ ድጋፍ አደረገች
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ጀርመን በኢትዮጵያ የሰሜኑ ክፍል እየተከናወነ ያለውን የመልሶ ማቋቋም ስራ ለመደገፍ ተጨማሪ የ4 ሚሊየን ዩሮ ድጋፍ ማጽደቋ ተገለጸ።
በዚህም ጀርመን ለሰላም ግንባታና መልሶ ማቋቋም ያደረገችው ድጋፍ 14 ነጥብ 1 ሚሊየን ዩሮ መድረሱ ተነግሯል።
ድጋፉ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል በነበረው ጦርነት ጉዳት በደረሰባቸው የአፋር፣ አማራ እና ትግራይ ክልሎች ውስጥ እየተከናወነ ለሚገኘው የመልሶ ማቋቋም ስራ የሚውል ነው ተብሏል፡፡
በኢትዮጵያ ተጠባባቂ የጀርመን አምባሳደር ፈርዲናንድ ቮን ዌይሂ ድጋፉን ለገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ሰመሪታ ሰዋሰው ባስረከቡበት ወቅት ሀገራቸው የምታደርገውን ድጋፍ እንደምታጠናክር ገልጸዋል።
በአካባቢው የተገኘውን ተስፋ ሰጪ ሰላም ለማፅናት ውይይት እና መተማመን አስፈላጊ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታዋ በበኩላቸው፤ በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለመገንባትና ለኑሮ ምቹ እንዲሆኑ ለማስቻል በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህ ረገድ የጀርመን መንግስት ወሳኝ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝም ገልጸዋል።