‹‹እልፍ አእላፍ መከራዎች፣ የተፈጥሮ አደጋዎች፣ሰው ሰራሽ ችግሮች ተደራርበው ያላስቆሙትን የኢትዮጵያ የብልፅግና ጉዞ ራዕይን ተሸክመን ዛሬ ላይ ደርሰናል።
በደም የተከበረውን ሉዓላዊነታችንን በላብ ለማፅናት እያደረግን ያለነው ተጋድሎ በሕዝባችን ሁለንተናዊ ድጋፍ ውጤታማነቱ ቀጥሎ ኢትዮጵያን ወደ ብልፅግና በሚያሻግሩ ስኬቶች ታጅበን ዛሬ ላይ መቆም ችለናል።
ኢትዮጵያ የሚያርፉባት የመከራ በትሮች ይበልጥ ፀንታ እንድትቆም አድርጓት፣ ሕዝቦቿ በፈተና መሀል አንድነታቸውን እንደ አለት ህብረታቸውን እንደ ብረት እያጠነከሩ አዲሱን 2017 አመት ለመቀበል ከጫፍ ደርሰናል።
ትናንት ያጋጠሙን ፈተናዎች የህዳሴ ግድብ ግንባታን ወደ ማጠናቀቂያ ምዕራፍ ከማድረስ፣ ዘርፈ ብዙ ጫናዎችን ከመሻገር፣ የስንዴ ፍላጎታችንን በሀገር ውስጥ በማሟላት ኤክስፖርት ማድረግ ከመጀመር፣ የአምራች ኢንዱስትሪ የተኪ ማምረት አቅም ከማጎልበት፣ ደረጃቸውን የጠበቁ የቱሪዝም መዳረሻዎችን ከመገንባት፣ በአጠቃላይ እልፍ አእላፍ ስኬቶችን ከማስመዝገብ አላገዱንምና ክብሩን ፈጣሪ ይውሰድ።
በመጪው አዲስ አመትም ከትናንት ፈተናዎች ተምረን፣ የመሻገር ጥሪቶችን የአዲስ ብርሃን ወረቶች አድርገን በአንደኛው የፓርቲያችን ታሪካዊ ጉባኤ ላይ ቃል እንደገባነው ከፈተና ወደ ልዕልና መሻገራችንን እና ሀገራችንንና ሕዝባችንን ወደ ብልፅግና ማሻገራችንን አጠናክረን እንቀጥላለን!!
መልካም ጳጉሜን 1 – የመሻገር ቀን!!››
የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት እና በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ አደም ፋራህ