የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ውጤት ይፋ ሆነ
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ውጤት ይፋ መሆኑን ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ተማሪዎቹ ውጤታቸውን ከሌሊቱ 6 ሠዓት ጀምሮ ማየት እንደሚችሉም ተገልጿል፡፡
የትምህርት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) በሰጡት መግለጫ÷የዘንድሮውን የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ለመውሰድ ከተመዘገቡ 701 ሺህ 749 ተማሪዎች መካከል 674 ሺህ 823 ተማሪዎች ፈተናውን ወስደዋል ብለዋል ።
ቀሪዎቹ በተለያዩ ምክንያቶችና ትምህርታቸውን ዘግይተው በመጀመራቸው ፈተናውን አለመውሰዳቸውን ገልጸዋል ።
ከተፈታኞቹ ውስጥ 29 ሺህ 736 ያህሉ ለመጀመሪያ ጊዜ በተሰጠው የኦንላይን ፈተና አማካኝነት ፈተናቸውን ወስደዋል ነው ያሉት፡፡
ዘንድሮ ፈተና ከወሰዱት አጠቃላይ ተማሪዎች ያለፉት 5 ነጥብ 4 በመቶ መሆናቸውን ጠቅሰው÷ አዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር እንዲሁም ሐረሪ እና ኦሮሚያ ክልሎች ከአስፈተኗቸው ውስጥ የተሻለ ቁጥር ማሳለፋቸውን ገልጸዋል፡፡
ሁሉም ክልሎች በአለፈው ዓመት ከአስፈተኗቸው ተማሪዎች ቁጥር አንጻር ዘንድሮ የተሻለ ማሳለፍ መቻላቸውንም ጠቅሰዋል፡፡
በመሳፍንት እያዩ እና የሻምበል ምኅረት