Fana: At a Speed of Life!

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ለ892 የሕግ ታራሚዎች ይቅርታ አደረገ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አዲስ ዓመትን ምክንያት በማድረግ ለ892 የሕግ ታራሚዎች ይቅርታ አደረገ፡፡

የክልሉ ርዕሰ መሥተዳድር ጥላሁን ከበደ እንደገለጹት÷ ይቅርታ የተደረገላቸው የሕግ ታራሚዎች በማረሚያ ቤት ቆይታቸው መልካም ሥነ-ምግባር ያሳዩ እና በሕግ በተደነገገው የይቅርታ መስፈርትን ማሟላታቸው በክልሉ የይቅርታ ቦርድ ተጣርቶ የቀረቡ ናቸው።

ታራሚዎቹ መደበኛ የይቅርታ ሕግ እና ሌሎች ተጨማሪ መስፈርቶችን የሚያሟሉ ተብለው በልዩ ሁኔታ የቀረቡ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡

በዚሁ መሰረት የይቅርታው ተጠቃሚዎች ይቅርታ በማያስከለክሉ ወንጀሎች ተሳትፈው በማረሚያ ቤት የቆዩ፣ በጤና ችግር፣ በዕድሜ መግፋትና ከሕጻናት ጋር አብረው የታሰሩ፣ ከተጎጂ ወገኖች ጋር ታርቀው የእርቅ ሰነድ ማቅረባቸው በየደረጃው በሚገኝ የፀጥታ መዋቅር በቂ ማረጋገጫ የተሰጣቸውን ታራሚዎች እንዲሁም ከተፈረደባቸው ሲሶ (1/3) እና ከግማሽ (1/2) በላይ የፍርድ ጊዜያቸውን ያጠናቀቁ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡

ይቅርታው ከተደረገላቸው 892 የሕግ ታራሚዎች መካከል 879 ከእስር የሚፈቱ ሲሆን÷ ቀሪ 13 ታራሚዎች የእስራት ጊዜያቸው የተቀነሰላቸው መሆኑን ርዕሰ መሥትዳድሩ ገልጸዋል።

የይቅርታ ተጠቃሚ ከሆኑት የህግ ታራሚዎች መካከል 831 ወንዶች ሲሆኑ 48 ደግሞ ሴቶች ናቸው ማለታቸውን የርዕሰ መሥተዳድር ጽ/ቤት መረጃ አመላክቷል፡፡

የይቅርታው ተጠቃሚ የሆኑ የሕግ ታራሚዎች ሰላም ወዳድ፣ ለሕግ ተገዥና አምራች ዜጋ በመሆን ሕብረተሰቡን በማገልግል በልማት ሊክሱ እንደሚገባም አሳስበዋል።

ሕብረተሰቡም በይቅርታ የተለቀቁት የሕግ ታራሚዎች በፈፀሙት ጥፋት የተፀፀቱና በአግባቡ ታርመው የወጡ መሆኑን በመረዳት መልካምና አምራች ዜጋ ይሆኑ ዘንድ አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.