የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር ለአዲስ ዓመት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜ 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር ለ2017 አዲስ ዓመት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በመልዕክታቸውም÷በአዲሱ ዓመት አብሮነታችንን ሊነጥሉን የሚከጅሉ አስተሳሰቦችን በማስወገድ በአመክንዮና በሰከነ አስተሳሰብ በመመራት የሕግ የበላይነት በጽኑ መሠረት ላይ እንዲገነባ በትኩረት መስራት ይገባል ብለዋል፡፡
አፈ-ጉባዔው ያስተላለፉት መልዕክት ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
እንኳን ለ2017 አዲስ ዓመት በሰላም አደረሳችሁ፣ አደረሰን!
እንቁጣጣሽ!
አዲሱ ዓመት የጀመርነውን የለውጥ ጉዞ በልህቀትና በምልዓት በማስቀጠል በአዲስ ወኔና ተስፋ ወደ ላቀ የከፍታ ምእራፍ የምንሻጋገርበት ዘመን ይሆናል!
በቅድሚያ ለሁሉም ለመላው የአገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እንኳን ለ2017 አዲስ ዓመት በሰላም አደረሳችሁ፣ አደረሰን እያልኩ አዲሱ ዓመት ከጨለማ ወደ ብርሃን፣ ከመገፋፋት ወደ መደጋገፍ፣ ከንትርክ ወደ ውይይት፣ ከጉስቁልና ወደ ብልጽግና የምንሻጋገርበት ዘመን እንዲሆንልን በራሴና በፌዴሬሽን ምክር ቤት ስም ከልብ እመኛለሁ፡፡
የክረምት ወራት ነጐድጓዳው የመብረቅ ድምፅ የሚሰማበት፤ የባሕርና የወንዞች ሙላት የሚያይሉበት፤ ጸሐይ በጥቁሩ የደመና ግርዶሽ የምትከለልበት፣ ውሽንፈር፣ ብርድ፣ ቅዝቃዜና ቁር የሚበረቱበት፣ የምድር ገጾች በጭጋግ የሚጋረዱበት፣ ገበሬው ብርዱን፣ ውርጭና ቁሩን ሳይሳቀቅ የእጁን ፍሬ ያገኝ ዘንድ በተስፋ የሚዘራበት ወቅት ነው፡፡
በሂደትም ምድር ከከረመው ብካይዋ ተላቃና ታድሳ፣ በአረንጓዴ ልምላሜ ተሞሽራና በኅብረ ቀለማት አበቦች ተሽቆጥቁጣ መታየት ትጀምራለች፡፡ የተዘራው ዘርም የሰው ልጅን ተስፋ ዳግም ለማለምለም ያድጋል፣ ያሸታል፣ ያፈራልም፡፡ በዚህ ዘመን ሽግግር የምንቀበለው የአዲስ ዓመት በዓል በመላው ኢትዮጵያዊያን ዘንድ ልዩ ትርጉም አለው፡፡
አዲስ ዓመት ዶፍና ውሽንፍሩ፣ በረዶና ቁሩ፣ ጎርፉና ማዕበሉ፣ ብርዱና ጠሉ ዐልፎ አበባዎች በምድር ላይ የሚታዩበትና ማእዛቸውን የሚሰጡበት፤ ወንዞችና ምንጮች የሚጠሩበት፣ ጠቁሮ የከረመው ሰማይ በብርሃን ጸዳል የሚፈካበት፣ ሜዳና ጋራው የመከር ጊዜ መድረሱን የሚያበስሩበት እና ልባችን በተስፋ ተሞልቶ ወደ አዲስ የሕይወት ምዕራፍ የምንሸጋገርበት እንደሆነ ሁሉ ያደሩ ሀገራዊ ችግሮቻችንን ፈትተንና የጀመርነውን የለውጥ ጎዞ አስቀጥለን ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን የምንመኘውን የዴሞክራሲ ሥርዓት እውን የምናደርግበት ዘመን ይሆናል፡፡
በመሆኑም በአዲሱ ዓመት ከአብሮነት አውዳችን ሊነጥሉን የሚከጅሉንን በካይ፣ ነጣይና አጣይ አስተሳሰቦችን በማስወገድ በአመክንዮና በሰከነ አስተሳሰብ በመመራት የሕግ የበላይነት በጽኑ መሠረት ላይ እንዲገነባ በትኩረት የምንሠራበት ዓመት ሊሆን ይገባል፡፡ በአሮጌው ዓመት ከዚያም ከዚህም ከታየው ደም አፋሳሽ የርስ በርስ ግጭት ተላቀን፣ የጽንፈኝነት የሽብትና የተነጣይነት ደመና ተገፎና የቂም በቀል ጎተራችን ተራግፎ እንደ አገርም በአዲስ ወኔና ተስፋ ወደላቀ ልዕልና የምንሻገርበት ዓመት እንዲሆን እየተመኘሁ የኢፌዴሪ ፌዴሬሽን ምክር ቤትም ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ ባካሄደው ተቋማዊ ሪፎርም በሕገ መንግሥቱ የተጣለበትን ተግባርና ኃላፊነት በላቀ ደረጃ ለመወጣት እየሠራ ይገኛል፡፡
በተለይም ምክር ቤቱ የብሔሮች፣ ብሔሮችና ሕዝቦች ውክልና ያለው ተቋም እንደመሆኑ መጠን ባለፉት ዓመታት በሕዝቦች እኩልነትና መፈቃቀድ ላይ የተመሠረተ ኅብረብሔራዊ አንድነት ስር እንዲሰድና የርስ በርስ ትስስሩ እንዲጎለብት ከፍተኛ ሥራዎች ሲሠራ ቆይቷል፡፡ ወደፊትም ትኩረት ሰጥቶት የሚሠራበት ዘርፍ ነው፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ምክር ቤቱ የቀረቡለትን የሕገ መንግሥት ትርጉም ውሳኔዎችን በመመርመርና በመወሰን ዜጎች ፍትሕ የማግኘት መብታቸው እንዳይጣበብና በሀገራችን ያለው የሕግ የበላይነት መሠረት እንዲይዝ ሰፋፊ ሥራዎችን ሠርቷል፡፡
ባለፉት ዓመታት ምክር ቤቱ በሀገር ውስጥና በውጭ ግንኙነት ዘርፍ በተሻለ ደረጃ በመሥራት ሀገራዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ግንኙነቶችን፣ ትብብሮችንና አጋርነቶችን ማጠናከር ችሏል፡፡ የሚያከናውናቸውን ተግባራት፣ የሚያካሂዳቸውን ውይይቶች፣ የሚወስናቸውን ውሳኔዎች የተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎችን በመጠቀም በግልጽ ለሕዝብ ተደራሽ እንዲሆኑ አድርጓል፡፡
በሕገ መንግሥቱ በተሰጠው ሥልጣንና ኃላፊነት መሠረት የክልሎችና የፌዴራሉ መንግሥት የጋራ ተብለው የተመደቡ ገቢዎች በሁለቱ መካከል የሚከፋፈሉበትን፣ እንዲሁም የፌዴራሉ መንግሥት ለክልሎች ድጎማ የሚሰጥበትን ቀመር ሲወስን የቆየ ሲሆን በክልሎች መካከል የተመጣጠነ እድገት እንዲኖር የፌዴራል ድጎማዎች ግልጽነት፤ ተጠያቂነትና ዘላቂነት ባለው መልኩ በፍትሐዊነት ለክልሎች የሚከፋፈልበት የአሠራር ሥርዓት በማሻሻል በርካታ ተግባራት አከናውኗል፡፡
በአጠቃላይ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በአዲሱ ዓመት ካለፉት ዓመታት ተሞክሮዎችን በመውሰድ የላቀ አፈጻጸም ለማስመዝገብ ያለውን ዝግጁነት እየገለጽኩ አዲሱ ዓመት ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሰላም፣ የፍቅር፣ የመቻቻል፣ የአንድነትና የብልጽግና ዘመን እንዲሆንላችሁ ከልብ እመኛለሁ፡፡