Fana: At a Speed of Life!

የሰላም፣ የመቻቻልና የብልፅግና ተምሳሌት የሆነ ክልል ለመንባት እንረባረባለን – አቶ ጥላሁን ከበደ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜ 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሰላም፣ የመቻቻልና የብልፅግና ተምሳሌት የሆነ ክልል ለመንባት እንረባረባለን ሲሉ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ገለጹ።

ርዕሰ መስተዳድሩ ለአዲስ ዓመት ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክት፤ በ2017 የላቀ አፈፃፀም ለማስመዝገብ ከሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ጋር በትብብርና በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አመልክተዋል።

በዚህም የሰላም የመቻቻልና የብልፅግና ተምሳሌት የሆነ ክልል ለመንባት የተጣለውን ግብ ለማሳካት እንረባረባለን ብለዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ጥላሁን ከበደ ለአዲስ ዓመት ያስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልካም ምኞች መግለጫ ሙሉ መልዕክት

መላዉ ኢትዮጵያን እንኳን ለአዲሱ ዓመት በሠላም እና በጤና አደረሰን! አደረሳችሁ!

አዲሱ ዓመት የሠላም የፍቅር የመቻቻልና የብልፅግና እንዲሆንላችሁ ልባዊ ምኞቴን እገልፃለሁ።

የተከበራችሁ የክልላችን ህዝቦች ከዛሬ 365 ቀናት በፊት አዲስ ዓመት ብለን የተቀበልነውን 2016 ዓ.ም በፈጣሪ ቸርነት ተሻግረን አሮጌው ብለን ለመሸኘትና 2017 ደግሞ አዲሱ ዓመት ብለን ለመቀበል እንኳን በሰላም አደረሰን።

በክልላችን የህብረተሰባችንን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በተከናወኑ ዘርፈ ብዙ ተግባራት ውጤት ማስመዝገብ ችለናል።

በተለይ በግብርና ዘርፍ በበጋ ስንዴ፣ በአረንጓዴ አሻራ፣ በሌማት ትሩፋትና በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ተግባራት ተስፋ ሰጪ ውጤቶች መታየትም ጀምረዋል።

በማህበራዊ ልማት የትምህርት ስብራትን ለመጠገን መላው ህዝባችንን አስተባብረን ባከናወነው ተግባር በትምህርት ልማት መሻሻሎች እየታዩ ይገኛል።

በክልሉ የተተገበረው የፍትህ ተቋማት ትራንስፎርሜሽን ተቋማቱ ገለልተኛ እንዲሆኑ ከማድረግ ባሻገር ህብረተሰቡ በተቋማቱ ላይ ያጣውን አመኔታ እንዲመለስ በማድረግ ላይ ነው።

በ2016 ዓ.ም ተደምረንና ተቀናጅተን ተግባራትን በመምራታችን በሁሉም ዘርፍ ስኬት ማስመዝገብ ብንጀምርም በአንዳንድ የክልላችን አከባቢዎች በተከሰቱ የተፈጥሮ አደጋዎች ወገኖቻችንን በሞት የተነጠቅን ሲሆን አደጋው ከአፈርና አከባቢ ጥበቃ አንፃር ያላከናወነው የቤት ስራ መኖሩን አመላክቶን አልፏል።

በአደጋው የተጎዱ ወገኖቻችንና ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን በዘላቂነት ለማቋቋም መላው ኢትዮጵያን ያደረጉት ድጋፍ ከጥንት ጀምሮ የነበረ፣ ያለና ወደፊትም የሚኖር ድንቅ የሆነ የመረዳዳት እና የመተጋገዝ ባህላችንን ለአለም አሳይቷል።

የተከበራችሁ የክልላችን ህዝቦች

መንግስት በ2016 በጀት ዓመት እንደ ክልል የገጠሙንን ወቅታዊ እና ጊዜያዊ ፈተናዎች ወደ ዕድል በመቀየር በ2017 የላቀ አፈፃፀም ለማስመዝገብ ከሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በጋራ ለመስራትና በቁርጠኝነት በማገልገል የሰላም የመቻቻልና የብልፅግና ተምሳሌት የሆነ ክልል ለመንባት የተጣለውን ግብ ለማሳካት እንረባረባለን።

ክልላችን በርካታ የኢንቨስትመንት አማራጮች ያሉት፣ ዘርፈ ብዙ የቱሪዝም መዳረሻዎች እና ሀብቶችን ያቀፈ ክረምት ከበጋ የሚፈሱ ወንዞችና ለም መሬትና የሰው ኃይል ያለው በመሆኑ እነዚህን ሀብቶች ከህዝባችን ጋር አስተሳስረን መምራት ከቻልን መጪው ጊዜ የተስፋ ፍንጣቂ የምናይበት ይሆናል።

ውድ የክልላችን ህዝቦች

በአዲሱ ዓመት ጥላቻንና መገፋፋትን አሽቀንጥረን በመጣል አብሮነትና አንድነትን በማጠናከር ለክልሉ ሁለንተናዊ ብልፅግና መረጋገጥ የድርሻችሁን እንድትወጡ ጥሪዬን አቀርባለሁ።

አዲሱ ዓመት መላው የክልላችን ህብረተሰብ ተጠቃሚነት ወደላቀ ደረጃ የሚሸጋገርበት እንዲሁም ህብረ ብሄራዊ አንድነታችን የሚያብብበት የስኬት ዘመን እንዲሆንላችሁ በድጋሚ እመኛለሁ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.