ሀገራዊ ጥበቦቻችን ተጠቅመን ኢትዮጵያን ወደ ብልፅግና ከፍታ እናሻግራት – አቶ ደስታ ሌዳሞ
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሀገራዊ እውቀቶቻችንን እና ጥበቦቻችን ተጠቅመን ኢትዮጵያን ወደ ብልፅግና ከፍታ እናሻግራት ሲሉ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ደስታ ሌዳሞ አስገነዘቡ፡፡
ርዕሰ መሥተዳድሩ የአዲስ ዓመት የእንኳን አደረሳችሁ የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በመልዕክታቸውም÷ የጀመርናቸው የእድገት ሪፎርሞች እና የልማት ውጥኖቻችን ወደ ብልፅግና የሚመሩን ናቸው ብለዋል፡፡
ሀገራዊ ጥሪቶቻችንን፣ እውቀቶቻችንን፣ ብልሀቶቻችንን፣ ጥበቦቻችንና ቅንነቶቻችንን ተጠቅመን እጅ ለእጅ ተያይዘን ጠንክረን በመሥራት ኢትዮጵያን ወደ ብልፅግና ከፍታ እናሻግራት ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡
የርዕሰ መሥተዳድሩ የመልካም ምኞት መግለጫ ሙሉ መልዕክት ቀጥሎ ቀርቧል፡-
በአዲሱ ዓመት እኛ ኢትዮጵያውያን አንድነታችንን አጠናክረን፣ ሰላማችንን ጠብቀን፣ ሙሉ አቅማችንና ጊዜአችን ለልማትና ለእድገት አዉለን እና ብሩህ ተስፋን ሰንቀን የሀገራችንን የብልጽግና ጉዞ በትጋት የምናያስቀጥልበት አመት ይሁንልን፡፡
እኛ ኢትዮጵያውያን አንድና የጋራ ራዕይና እሴት ያለን ህዝቦች ስንሆን እሱም ሀገራችን በሁለንተናዊ አድጋና በልፅጋ ከድህነት ተላቃ ማየት ሲሆን የለውጡ መንግስት ይህን እውን ለማድረግ በትጋት እየሰራ ይገኛል።
ይህ ህልማችን እውን እየሆነ መሄዱን የሚያሳዩ በለውጡ መንግስት የተመዘገቡ በርካታ የልማት ድሎቻችን አመላካች እየሆኑ መጥተዋል ። እነዚህን የልማት ድሎቻችንን ለማስመዝገብ የቻልነው በርካታ ውስብስብ ፓለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጫናዎችን በድል ተሻግረን ነው ።
ባለፉት የለውጥ አመታት ሀገር አፍራሽ ተልዕኮን ያነገቡ ግጭቶችንና ጦርነቶች በአሸናፊነት ተሻግረን የሀገር ህሊና አረጋግጠን፤ ሉዓላዊነትን የሚፈታተኑ የውጭ ፖለቲካ ጫናዎችን በጥበብና በበሳል ዲፕሎማሲያዊ መንገዶች አልፈን፤የተጋረጡብንን ችግሮች በብልሃት መፍታት ችለናል።
ነገር ግን ይህ ሁሉ ሀገራዊ ፈተናዎች አንገታችንን አላስደፉንም ይበልጥ አጠነከሩን እንጂ ፤ በችግሮች ሳንበገር በርካታ የልማት ድሎችን ያስመዘገብን ሲሆን በአስገራሚ ፍጥነት ታላላቅ ሜጋ ፕሮጀክቶችን ገንብተን ለህዝብ ጥቅም ላይ ማዋል ችለናል ።
በተጨማሪም የታላቁን ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ አጠናቀን ኃይል ወደ ማመንጨት የመሻገር ምዕራፍ ላይ መድረሳችን እና ገበታ ለሀገርን ጨምሮ የቱሪዝም ኢንዱስትሪያችንን ለማበልፀግ በርካታ የቱሪዝም መዳረሻ ማዕከላትን በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች መገንባት መቻላችን ለአብነት ያህል መንግሥታችን በቅልጥፍና ያከናወናቸው ልማቶች ትርፋቶች ናቸው ብሎ መጥቀስ ይቻላል ።
ሀገራችንን ከበለጸጉ ሀገሮች ተርታ ለማሰለፍ ሀገራዊ የልማት ሪፎርሞችን አድረገን በርካታ ለዉጦች ማስመዝገብ ችለናል።መንግሥታችን የቅድም ቅድምያ ሰጥቶ የግብርና ስርዓቱን በማዘመን የምግብ ዋስትናችንን ለማረጋገጥ በርካታ ስራዎችን የሰራ ሲሆን በዚህ አመርቂ ውጤት በማምጣት ከተረጅነት ተላቀን የስንዴ ምርትን ለውጭ ገበያ ማቅረብ መቻላችን አንዱ አስደማሚ የልማት ቱሩፋታችን ነው።
የስንዴ ምርትን በዘመናዊ መንገድ በዓመት ሦስት ጊዜ በመኸር በበጋና በመስኖ በማምረት የሀገር ውስጥ ፍጆታን መሸፈን ከመቻሉ በተጨማሪ የአርሶ አደሩን የኢኮኖሚ አቅምን ከመገንባት ረገድም ተአምራዊ ለዉጦች መጥተዋል ።
በከተሞች ግንባታና እድገት ላይ ትውልዳዊ አሻራውን ለማኖር እንዲሁም ከተሞቻችን ከኋላቀርነትና ከጉስቁልና ተላቀው በአለም አቀፍ ስታንዳርድ ደረጃቸውን የጠበቁ ፅዱና ዘመናዊ ለነዎሪዎች ምቹ ሆነው እንዲገነቡ ለማድረግ የከተሞች ግንባታ ሪፎርም በማድረግ የኮሪደር ልማት ግንባታዎች በማከናወን አስደሳችና ላቅ ያሉ ውጤት አስመዝግቧል። በቀጣይ አመታትም ህዝቡን ተጠቃሚና የሚያደርጉ ጉዙፍ ሜጋ ፕሮጀክቶች ለመገንባት ታቅደው እየተሰሩ ይገኛሉ።
ላለፉት የለዉጥ ዓመታት ውስብስብ የሀገር ውስጥና የውጭ ፖለቲካዊ ጫናዎቻችንን በድል መውጣት ብቻ ሳይሆን እንደ ሀገር ህልውናችንንና ሉዓላዊነታችንን ለማስቀጠል በሳል የዲፕሎማሲ አቅማችን ብቻ በቂ ባለመሆኑ በዘመኑ ዓለም በደረሰበት መከላከያና ደህንነት ተቋሞቻችን በዕውቀት ፤በአካል ብቃት፤ስነልቦና፤ ቴክኖሎጂ በመገንባት ሀገራችንን የሚመጥን ለማድረግ ተችሏል።
በቀጣይ ጊዜያት ኢንቨስትመንትን በላቀ ደረጃ ለማስቀጠልና የኢኮኖሚ አቅማችንን ለማጎልበት እንዲረዳን፤ ተቋማት ተልዕኮዋቸውን በተገቢው መንገድ እንዲወጡ አስተማማኝ የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን ለማካሄድ ፤የግብርና ኢኮኖሚውን ለማዘመንና አምራች አርሶ አደሮችን በመደገፍ የኢኮኖሚ አቅማቸው ከማሳደጉ በተጨማሪ በምግብ ሰብል ሙሉ በሙሉ ራሳችንን ለመቻል እንዲያስችለን ፤እንዲሁም የዕዳ ጫናዎቻችንን ለመቀነስ፤የዉጪ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ እና የሀገር ምርት ለማበረታታት የሚፈለገውን ሀገራዊ እድገታችንን ለማሳለጥ የማይክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲያችንን ተግባራዊ እያደረግን እንገኛለን።
ሁሉም ሀገር ወዳድ ዜጋ ፥ነጋዴው ማህበረሰብ፥ አርሶ አደሩ፥ ኢንቨስተሩ ፥ሰራተኛውና የሚመለከታቸው ባለ ድርሻ አካላት ይህ ማይክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ በተገቢው መንገድ ውጤታማ እንዲሆን በታማኝነትና በቅንነት ከመንግስት ጎን ቆመው እንዲሰሩ ለማሳሰብ እወዳለሁ።
ሁሉም የኢትዮጵያ ብሔሮች ለሀገራችን ድምቀትና ውበት ናቸው። ቋንቋችን ፥ ባህላችን፥ የአኗኗ ስርዓታችን ፥ብዝሃ ኃይማኖታችን ዉብ ህብር ናቸው ። የማንነታችን ብዝሃነት የህብሬ ብሔራዊት አንድነትና ጥንካሬያችን ማሳያ ነው ። የህብረ ብሔራዊ አንድነታችን በወንድማማችነትና እህትማማችነት መዋደድና መከባበር ላይ የተመሰረተ በመሆኑ አንዳችን ላንዳች ካስማና ማገር ሆነን ህብረብሔራዊ ኢትዮጵያን አልቀን ለዘመናት አዝልቀንና አሻግረን እዚህ ደርሰናል ።
ሆኖም ግን ታሪካዊ የኢትዮጵያ ጠላቶች ይህን ብዝሃነታችንንና አንድነታችንን በሀሰተኛ ትርክቶች አንድነታችን ለመናድ በርካታ ፓለቲካዊ ሴራዎችን ሸርቦብናል።
ነገር ግን እነዚህ ሀገራዊ ፈተናዎች ያልበገረን ኢትዮጵያዊ አንድነታችንን ሊንዱ ያልቻሉት ብዝሃነታችን ኃይላችንና ጥንካሬያችን ምንጭ በመሆኑ ነው ።
እነዚህ ድንበር ዘለል ይሁኑ ሀገራዊ ችግሮቻችንን ከመሠረቱ ማድረቅ ና ስር ነቀል ሀገራዊ ለውጥ ማምጣት የሚቻለው ሀገራዊ ምክክር በማድረግ በመሆኑ የኢትዮጵያ የምክክር ኮሚሽን በሁሉም ክልሎች ሀገራዊ ምክክር አጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ጀምሯል። ችግሮቻችንን መፍታት የምንችለው በመደማመጥ ስንነጋገር ስለሆነ አሁን በያዝነው ሀገራዊ ምክክር ሁሉም ኢትዮጵያዊ ንቁ ተሳታፊ በመሆን አንዲተጋ ጥሪ ለማቅረብ አወዳለሁ።ለውጤቱ ማማር ሁሉም ኢትዮጵያዊ ኃለፊነቱን እንዲወስድ አሳስባለሁ።
የጀመርናቸው የእድገት ሪፎርሞች እና የልማት ውጥኖቻችን ወደ ብልፅግና የሚመሩን ናቸው።ሀገራዊ ጥሪቶቻችንን ፥ እውቀቶቻችንን፥ብልሀቶቻችንን ፥ ጥበቦቻችንና ቅንነቶቻችንን ተጠቅመን እጅ ለእጅ ተያይዘን ጠንክረን በመሥራት ሀገራችንን ወደ ብልፅግና ከፍታ እናሻግራት እላለሁ።
በድጋሚ አዲሱ አመትውጥናችንን የምናሳካበት የደስታ ዘመን እንዲሆንልን እየተመኛሁ በዓሉን ያለን ለሌላቸው እያካፈልን በመረዳዳትና በመደጋገፍ በዓሉን በደስታ እናክብረው እላለሁ !!