ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ትብብር ማጠናከር እንደምትፈልግ ገለፀች
አዲስ አበባ፣ መስከረም 3፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የልማት ትብብር አጠናክራ መቀጠል እንደምትፈልግ የሀገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
በሚኒስቴሩ የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ዱ ዢአዎሂ በሰጡት መግለጫ÷ የአፍሪካ-ቻይና ጉባዔ ትብብሩን ለማሳደግ የሚያስችሉ እድሎችን ማስገኘቱን ጠቅሰዋል፡፡
ቻይና የአፍሪካን ልማት መደገፏንና ለጋራ ተጠቃሚነት መሥራቷን አጠናክራ እንደምትቀጥልም አረጋግጠዋል፡፡
በዚህ ማዕቀፍ ከኢትዮጵያ ጋር የተለያዩ ስምምነቶች መኖራቸውን ገልጸው÷ ቻይና የኢትዮጵያን የ10 ዓመታት የልማት ዕቅድ ትደግፋለች ብለዋል።
በኢትዮጵያ፣ ቻይናና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት (ዩኒዶ) መካከል ባለፈው ሐምሌ ወር የተፈረመው የሦስትዮሽ ስምምነት እየተተገበረ መሆኑንም ነው ያነሱት፡፡
ስምምነቱ በአኅጉሪቱ የመጀመሪያ መሆኑን በመግለጽ ይህም የዘላቂ ወዳጅነት ማሳያ ስለመሆኑ አስረድተዋል።
የልኅቀት ማዕከል እንደተቋቋመ አንስተው÷ ፕሮጀክቱ የአፍሪካን የኢንዱስትሪ ልማት፣ የዘመናዊነት እድገትን ለመደገፍ ያለመ መሆኑንን አብራርተዋል፡፡
በስምምነቱ መሠረት በግብርና፣ በሰው ኃይል ስልጠና፣ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የ2030 የዘላቂ ልማት አጀንዳ፣ የአፍሪካ ኅብረት አጀንዳ 2063 እና የኢትዮጵያ የእድገት ውጥኖች መሳካት ላይ ትኩረት እንደሚደረግም አመላክተዋል፡፡
በአፈወርቅ እያዩ