ለጎርፍና መሬት መንሸራተት አደጋዎች ምላሽ ለመስጠት የተቀናጀ አሰራርን ለማጠናከር የሚያስችል ውይይት ተካሄደ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 3፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ለጎርፍና መሬት መንሸራተት አደጋዎች ምላሽ ለመስጠት የተቀናጀና የተናበበ አሰራርን ለማጠናከር የሚያስችል ውይይት ተካሄደ።
የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን በኢትዮጵያ በሰብዓዊ ዕርዳታ ስራ ላይ ከተሰማሩ አጋር አካላት ጋር በወቅታዊ የአደጋ ስጋት ምላሽ ዙሪያ ውይይት አካሂዷል፡፡
በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት እየተከሰቱ የሚገኙ የጎርፍና የመሬት መንሸራተት አደጋዎች ላይ በሚሰጡ ምላሾች ዙሪያ የተቀናጀና የተናበበ አሰራርን በፌደራልና በክልል ደረጃ ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑ በምክክሩ ወቅት አጽንኦት ተሰጥቶታል ተብሏል፡፡
መንግስትና አጋር አካላትም የቴክኒክና ሰብዓዊ ድጋፍ የትብብር ማዕቀፍ እንዲከተሉና ውጤታማ እንዲሆኑ መደረጉ ተገልጿል።
እንዲሁም በቀጣይ የበልግና የበጋ ወቅቶች ከወቅታዊ ምላሽ ጎን ለጎን ጉዳት ለመቀነስ የሚያስችሉ እርምጃዎች ከወዲሁ እንዲወሰዱ መግባባት መደረሱን ነው ከኮሚሽኑ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡