ተቋሙ በበጀት ዓመቱ 5 ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ እየሠራ መሆኑን አስታወቀ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 4፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በ2017 በጀት ዓመት የኃይል ማስተላለፊያ እና ማከፋፈያ ጣቢያዎችን ጨምሮ አምስት ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ እየሠራ መሆኑን አስታወቀ፡፡
የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ እንዳሉት÷ የአላማጣ – ኮምቦልቻ – ለገጣፎ ባለ 230 ኪሎ ቮልት 2ኛ ሰርኪዩት ዝርጋታ፤ የበቆጂ እና ደብረ ታቦር ማከፋፈያ ጣቢያ፤ የኮተቤ ግቢ ዕድሳት እና ማሻሻያ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ እየተሠራ ነው፡፡
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ዕድሳት እና የማሻሻያ ሥራንም ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅ እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
የደቡባዊ ግሪድ ማስፋፊያ እና የገዳ ስፔሻል ኢኮኖሚ ዞን 230 ኪሎ ቮልት የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ ፕሮጀክቶችን 75 በመቶ ለማድረስ እንደሚሠራ መግለጻቸውን የተቋሙ መረጃ አመላክቷል፡፡
በሌላ በኩል የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ 99 ነጥብ 4 በመቶ፣ የኮይሻ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት 73 ነጥብ 96 በመቶ፣ የአይሻ ንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክትን 95 ነጥብ 58 በመቶ ለማድረስ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
ፕሮጀክቶቹ አገልግሎት መስጠት ሲጀምሩ የኃይል መቆራረጥን ከመቀነስ ባሻገር የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽነትን እንደሚያሳድጉ አስረድተዋል፡፡