Fana: At a Speed of Life!

ለአካል ጉዳተኞች ኮሮናን ለመከላከል እንዲያግዝ 320 ሺህ ብር የሚገመት የቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 19፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች እና የልማት ማዕከል (ኢ ሲ ዲ ዲ) ጋር በመተባበር ድጋፍ የአካል ጉዳተኞች የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል የሚያግዝ 320 ሺህ ብር የሚገመት የንፅህና መጠበቂያ እና የምግብ ግብዓት ድጋፍ አድርገዋል፡፡

በዚህም ለችግር ተጋላጭ ለሆኑ 200 አካል ጉዳተኞች የምግብ ግብዓትና የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ድጋፍ የተደረገ ሲሆን ለ400 አካል ጉዳተኞች የሚሆን የንፅህና መጠበቂያ እና የፊት ማስክ የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ብሔራዊ ማህበር ፌዴሬሽን ተረክቧል፡፡

የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ አካል ጉዳተኞች በተለያዩ ምክንያቶች ለኮሮና ቫይረስ ይበልጥ ተጋላጭ መሆናቸውን አንስተው እየተደረገ ያለው ድጋፍ በቂ ባይሆንም ተደጋግፎ ይህን ክፉ ጊዜ ማለፍ እንደሚቻል መልዕክት ማስተላለፍ ያስችላል ብለዋል፡፡

ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር በመተባበር ድጋፍ ላደረገው ማእከል ምስጋና ያቀረቡት ሚኒስተሯ ድጋፉ ቀጣይነት እንደሚኖረው ገልፀዋል፡፡

የኢሲዲዲ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ መላኩ ተክሌ በበኩላቸው አካል ጉዳተኞችን ማካተት ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ እንዳልሆነ ጠቅሰው ከኮሮና ጋር በተያያዘ 5 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር የሚገመት ድጋፍ መደረጉን እና ድጋፉ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ብሔራዊ ማህበር ፌዴሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ አባይነህ ጎጆ ድጋፉ ወቅታዊና ለአካል ጉዳተኛው መድረስ ያለበት መሆኑን ጠቁመው ለእገዛው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱንና ማእከሉን ማመስገናቸውን ከሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል ፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.