የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ካፒታል 709 ቢሊየን ብር ደረሰ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 6፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አጠቃላይ ሀብት 709 ቢሊየን ብር መድረሱን በተቋሙ የፋይናንስ ዘርፍ ሥራ አስፈፃሚ ደመረ አሰፋ አስታወቁ፡፡
እንደ ሥራ አስፈጻሚው ገለጻ ከ709 ቢሊየን አጠቃላይ ሀብት መካከል 586 ቢሊየን ብሩ የተከፈለ ካፒታል ነው፡፡
ተቋሙ በመንግሥት እና በራሱ ባከናወናቸው የኢኮኖሚ ሪፎርም ትግበራ የተቋሙን ዕዳ ከ55 በመቶ ወደ 20 በመቶ ዝቅ ማድረግ መቻሉን አንስተዋል፡፡
ከአጠቃላይ ሀብቱ ከፍተኛ መዋዕለ-ንዋይ የወጣባቸው የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች 28 በመቶ ድርሻ ያላቸው መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
25 ነጥብ 5 በመቶው አጠቃላይ ሀብት ደግሞ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች፣ የከፍተኛ የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች እና የስዊች ያርድ ድርሻ መሆኑን ጠቅሰው የ150 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ዋጋ ያላቸው ናቸው ብለዋል፡፡
ቀሪው 46 ነጥብ 5 በመቶ ሀብት ተሽከርካሪዎች፣ ሕንጻዎች እንዲሁም ሌሎች ቋሚ እና ተንቀሳቃሽ ንብረቶችን ያጠቃለለ ነው ማለታቸውን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል መረጃ አመላክቷል፡፡
ተቋሙ በ2006 ዓ.ም እንደ አዲስ ሲቋቋም 34 ነጥብ 768 ቢሊየን ብር የተከፈለ ካፒታል በመያዝ እንደነበር አስታውሰው÷ ይህ አሃዝ በብዙ እጥፍ በማደጉ አዋጁን ማሻሻል እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከ19 በላይ የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች፣ 20 ሺህ ኪሎ ሜትር ርዝመት ያላቸው የከፍተኛ ኃይል ማስተላለፈያ መስመሮች፣ ከ144 በላይ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች በርካታ ሕንጻዎች እና ከ900 በላይ ተሽከርካሪዎች እንዳሉት ተገልጿል፡፡