በየነ ጴጥሮስ (ፕ/ር) የሰላማዊ ፖለቲካ ትግል ምልክት ነበሩ – ጠ/ሚ ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ መስከረም 7፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በየነ ጴጥሮስ (ፕ/ር) በኢትዮዽያ ገንቢ የፖለቲካ ባህል ለመፍጠር ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረከቱ የሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ምልክት ነበሩ ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
በየነ ጴጥሮስ (ፕ/ር) በአደረባቸው ህመም ምክንያት በሕክምና ሲረዱ ቆይተው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በአስተላለፉት የሐዘን መግለጫ መልዕክትም÷ “ያቆዩት ውርስ እና ቅርስ ፀንቶ እንዲቀጥል ነፍሳቸውም በሰላም እንድታርፍ እመኛለሁ” ብለዋል::
በየነ ጴጥሮስ (ፕ/ር) ጳጉሜን 4 ቀን 2012 ዓ.ም የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተሹመው ሲያገለግሉ መቆየታቸው ይታወሳል፡፡
በኢትዮጵያ ለበርካታ ዓመታት በፖለቲካ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ከቆዩ አንጋፋ ሰዎች መካከል አንዱ መሆናቸው የሚነገርላቸው በየነ ጴጥሮስ (ፕ/ር)÷ የተፎካካሪ ፓርቲው የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራሲ ፓርቲ ሊቀ-መንበር ሆነው ማገልገላቸው ይታወቃል፡፡
የተለያዩ ፓርቲዎችን በአባልነት የያዘውን የመድረክ ፓርቲንም በሊቀ-መንበርነት የመሩ ሲሆን÷ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲም በመምህርነት እንዲሁም በትምህርት ሚኒስትር ዴዔታነት ማገልገላቸው የሚታወስ ነው፡፡