Fana: At a Speed of Life!

የአፍሪካ የአካባቢ ሚኒስትሮች ጉባኤ ኢትዮጵያ ልምዶቿን ያካፈለችበት መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 8፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በኮትዲቯር አቢጃን በተካሄደው 10ኛው የአፍሪካ የአካባቢ ሚኒስትሮች ጉባኤ ኢትዮጵያ በርካታ ልምዶቿን ያካፈለችበትና ልዩ ልዩ ውሳኔዎች የተላለፉበት መሆኑን የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

“የመሬት መራቆትንና በረሃማነትን ለመዋጋት የሚያስችሉ ተግባራትን ለማፋጠን ተነሳሽነትን ማሳደግ” በሚል መሪ ሐሳብ የተካሄደውን የሚኒስትሮች ጉባኤ አስመልክቶ ሚኒስቴሩ በሰጠው መግለጫ፤ ኢትዮጵያ የአፍሪካ የአካባቢ ሚኒስትሮች መሪ መሆኗን አስታውሷል።

በመሆኑም ልዩ ጉባኤው እንዲዘጋጅ ከተወሰነ ጊዜ አንስቶ የጉባኤው ሴክሬታሪያት ከሆነው የተባበሩት መንግስታት የአካባቢ ፕሮግራም ጋር አስፈላጊውን መመሪያ በመስጠት አስፈላጊውን የሰነድና የሎጂስቲክስ ዝግጅት ስታደርግ ቆይታለች፡፡

በጉባኤው በርካታ ውሳኔዎች እንደተላለፉ፣ የመጀመሪያው “የአቢጃን ውሳኔ” የሚል ስያሜ እንዳለው፣ የአፍሪካን በረሐማነት፣ የመሬት መራቆትን እና ድርቅን የመቀነስ ፍላጎት ማሳደግ እንዲሁም የመሬት መራቆትን መግታት፣ በረሃማነት መከላከልና ድርቅን መቋቋም ዙሪያ ላይ ውሳኔዎች እንደተላለፉ በመግለጫው ተጠቅሷል፡፡

የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ፣ የብዝሀ ሕይወት፣ የበረሃማነት መከላከል እና የፕላስቲክ የተደራዳሪዎች ቡድኖች የአፍሪካን ፍላጎት በአግባቡ በአንድ ድምጽ በማሰማት የአህጉሪቱን ጥቅሞች እንዲያስጠብቁ፣ አፈጻጸማቸውን በቀጣዩ 20ኛው የአፍሪካ የአካባቢ ሚኒስትሮች ጉባኤ እንዲያቀርቡ አቅጣጫ መቀመጡም ተገልጿል።

በጉባኤው የተደረሱ ውሳኔዎች የወቅቱ የጉባኤው ፕሬዚዳንት በሆነችው ኢትዮጵያ በኩል በአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን በማቅረብ ለአፍሪካ መሪዎችን ለውሳኔ እንዲቀርብ ተጠይቋል።

በጉባኤው ኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ ልምዷን ያጋራችበትና በመድረኩም አድናቆት የተቸረው መሆኑን የሚኒስቴሩ መግለጫ አስታውቋል።

በታሪኩ ወ/ሰንበት

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.