አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከ500 በላይ ውጤት ላመጡ 200 ተማሪዎች ነጻ የትምህርት ዕድል ሰጠ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 8፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) አንጋፋው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በዘንድሮው የ12ኛ ክፍል ፈተና ከ500 በላይ ውጤት ላመጡ 200 ተማሪዎች ነጻ የትምህርት ዕድል መስጠቱን አስታወቀ፡፡
ዩኒቨርሲቲው ራስ ገዝ መሆኑን ተከትሎ በራሱ የቅበላ ሥርዓት ተቀብሎ ለማስተማር ምዝገባ እያከናወነ መሆኑንም አስታውቋል፡፡
በቅርቡም ያዘጋጀውን የተማሪዎች መግቢያ ፈተና እንደሚሰጥና ብቃትን፣ ብዝኀነትንና ፍትሐዊነትን ማዕከል አድርጎ እንደሚቀበል በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ገልጿል፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘ በ2016 የትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ፈተና ወስደው 500 እና ከዚያ በላይ ውጤት ያዝመዘገቡ 200 ተማሪዎችን በውድድር ነፃ የትምህርት እድል ከመኝታና የካፌ አገልግሎት ጋር እንደሚሰጥ አስታውቋል፡፡
ይህም ዩኒቨርሲቲው ብቃትና ተሰጥዖ ያላቸው ተማሪዎች መዳረሻ ለመሆን ያለውን ቁርጠኝነት እንደሚያሳይ ነው የገለጸው፡፡