Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ በመጭዎቹ ሁለት ሳምንታት የግድቡን ቀሪ የግንባታ ስራዎች በማጠናቀቅ የውሃ ሙሌት እንደምትጀምርና በእነዚህ ጊዜያት ሃገራቱ ከስምምነት ለመድረስ መወሰናቸው ተገለጸ

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 20 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በመጭዎቹ ሁለት ሳምንታት የታላቁ የህዳሴ ግድብ ቀሪ የግንባታ ስራዎች በማጠናቀቅ የውሃ ሙሌት እንደምትጀምርና በእነዚህ ሁለት ሳምንታትም ሃገራቱ ከስምምነት ለመድረስ መወሰናቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

ፅህፈት ቤቱ ባወጣው መግለጫ በትናንትናው እለት በአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ የህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት እና ውሃ አለቃቀቅ ደንብ ላይ በኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብጽ እየተካሄደ ባለው ድርድር ዙሪያ ምክክር መደረጉን አስታውሷል፡፡

በወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ በተጠራው በዚህ ስብሰባ ከሶስቱ ሃገራት በተጨማሪ የጉባኤው አባል የሆኑት ኬንያ፣ ማሊ እና ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ መሪዎች መገኘታቸውን ጠቅሷል፡፡

መሪዎቹ የናይል እና የታላቁ ህዳሴ ግድብ ጉዳይ የአፍሪካ ጉዳይ በመሆኑ ከአፍሪካ የሚመነጭ የመፍትሄ ሃሳብ እንደሚያስፈልገው ማንሳታቸውንም ገልጿል፡፡

በዚህ ረገድም የግድቡ ድርድር ስላለበት ሂደት ከኢትዮጵያ፣ሱዳን እና ግብጽ መግለጫዎች ቀርበው በቀጣይ ስለሚኖረው ሂደት አቅጣጫ ተቀምጧልም ነው ያለው፡፡

በዚህም በግድቡ ሙሌት እና አስተዳደር ላይ የሚደረገው ድርድር በሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት እንዲጠናቀቅም ከስምምነት መድረሳቸውንም ፅህፈት ቤቱ አስታውቋል፡፡

በተጨማሪም የአፍሪካ ህብረት ጉዳዩን መመልከት መጀመሩ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት እንዲገለጥ የአፍሪካ ህብረት እና የመሪዎች ጉባኤ ቢሮ አባላት ድርድሩን እንዲደግፉ ኢትዮጵያ ፣ ሱዳን እና ግብጽ ከቃላት መካረር እና አላስፈላጊ መግለጫዎች እንዲቆጠቡ አቅጣጫ ተቀምጦ ልዩ የመሪዎች ስብሰባ መጠናቁንም ነው የገለጸው፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.