በኦሮሚያ ክልል የቱሪዝም ሳምንት በተለያዩ ሁነቶች ይከበራል
አዲስ አበባ፣ መስከረም 10፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ኦሮሚያ ክልል የቱሪዝም ሳምንት ከመስከረም 21 እስከ 23 ቀን 2017 ዓ.ም በተለያዩ ሁነቶች እንደሚከበር ተገለጸ።
የቱሪዝም ሳምንቱን አስመልክቶ መግለጫ የሰጡት የክልሉ ቱሪዝም ኮሚሽን ኮሚሽነር ሌሊሴ ዱጋ፤ ቱሪዝምና ሰላም ላይ የውይይት ፎረም እንደሚካሄድ ተናግረዋል።
የቱሪዝም ሀብት የሚተዋወቅበት ዐውደ ርዕይ ከሁነቶቹ መካከል አንዱ መሆኑንም ገልጸዋል።
ለቱሪዝም ሀብት እድገት የጎላ አስተዋፅኦ እያደረጉ ያሉ ግለሰቦች እና ተቋማት እውቅና እንደሚሰጣቸው ጠቁመው፤ ወይዘሪት ቱሪዝም ኦሮሚያ ውድድርም በቱሪዝም ሳምንቱ የሚጠበቅ ሁነት መሆኑን ጠቁመዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህል፣ ቱሪዝም እና ኪነጥበብ ቢሮ ምክትል ሀላፊ አቶ ሀፍታይ ገ/እግዚያብሔር በበኩላቸው ለመስቀል ደመራ እና ለኢሬቻ በዓላት ድምቀት የከተማ አስተዳደሩ የበኩሉን እንደሚወጣ ተናግረዋል።
የሸገር ከተማም የከተማውን ብራንድ እና የቱሪዝም ሀብቱን ለማስተዋወቅ እየሰራ ነው ብለዋል የከተማ አስተዳደሩ ቱሪዝም ፅህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ቢኒያም ፀጋዬ።
በማርታ ጌታቸው